አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
በዚህ የዑለማዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለን ጨምሮ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ዑለማዎች፣ የክልል መጅሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የተለያዩ ጉዳዮች የተካተቱበት የመግባቢያ ሰነድ ላይ፣ የክልል ዑለማዎች ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ላይ ውይይት ይደረጋል።
ጉባኤው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በውስጡም የተለያዩ ተቋማዊ፣ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ የሥራ አፈጻጸሞችና ዕቅዶች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በጀማል አህመድ

