Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመደመር መንግሥት ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ ብልጽግና እየሠራ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)የመደመር መንግሥት ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ ብልጽግና እየሠራ ነው አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአባላትና የአደረጃጀት ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ያላቸውን አቅም ወደ ጠንካራ ተቋማዊ ብቃት በመቀየር በሕዝብ ኑሮ ላይ በሚያመጡት ተጨባጭ ለውጥ መመዘን አለባቸው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ የሚያፈልቁ፣ መሪዎችን የሚያፈሩና ከምርጫ ውድድር በኋላም የልማት ሥራዎችን የሚያስቀጥሉ ተቋማት መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ በመደመር ፍልስፍና የተለያዩ ሰዎችን፣ ተቋማትንና አቅሞችን በጋራ ዓላማ ዙሪያ በማሰባሰብ ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ ብልጽግና እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
ፓርቲው ከተለያዩ ክልላዊ መሠረቶች የመጡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በማምጣት የጋራ ዜግነትን ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ፓርቲው ከ16 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ አባላትና በመላ ሀገሪቱ የተዘረጉ መዋቅሮች እንዳሉት ጠቅሰው፤ የአባላትና የአደረጃጀት ብዛት ወደ ተቋማዊ ጥንካሬ እንዲቀየር ቀጣይነት ያለው የአመራርና የአባላት አቅም ግንባታ፣ የውስጥ ዴሞክራሲና ተጠያቂነት ወሳኝ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፓርቲው የአፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት ብቃትንና ታማኝነትን ለማበረታታት፣ ድክመቶችን ለመለየትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
የአፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት የአህጉሪቱን እምቅ ሀብትና አቅም ወደ ምርታማነት በመቀየር ላይ እንደሚመሠረት አንስተዋል፡፡
ፓርቲዎች ግልጽ አቅጣጫ በማስቀመጥ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ የሰው ኃይልን በማብቃትና ዘላቂ ዕድገትን የሚደግፉ ተቋማትን በማጠናከር የላቀ ሚና መጫወት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በሌሎች የውይይት መድረኮች ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የመጡ ከ275 በላይ መሪዎችን በተለያዩ የሕዝብ ኃላፊነቶች ላይ ማሳተፍ መቻሉንም ጠቅሰዋል።
ጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሞክሮና ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣ የሴቶችን፣ የወጣቶችን፣ የምሁራንንና የሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን ድምፅ የሚያካትት መድረክ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
በመሳፍንት ብርሌ
Exit mobile version