አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአባያ-ጫሞ ተፋሰስ ወንዞች ላይ የጎርፍ ትንበያ ማከናወን የሚያስችል አስተማማኝ የመረጃ ፍሰት ስርዓት ተዘርግቷል አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡
በሚኒስቴሩ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከልና አስተዳደር ፕሮጀክት በአባያ-ጫሞ ንዑስ ተፋሰስ የተከናወኑ ሦስት መሠረታዊ የጥናት ሪፖርቶችን እየገመገመ ነው ።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ተወካይ አቶ ተስፋዬ አባቡ እንደገለጹት፥ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የውሃ ሀብት አስተዳደር ከድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪነት ወደ ቅድመ ተከላካይና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አሰራር ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሳይንሳዊ ምርምሮችን ከተግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በማጣመር የሀገሪቱን የውሃ ደህንነት ማረጋገጥ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።
መረጃ በሌላቸው በአባያ-ጫሞ እና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ የጎርፍ ትንበያ መስራት የሚያስችል አስተማማኝ የመረጃ ፍሰት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተፋሰሶቹ ውስጥ የተቀናጀ የውኃ ሃብት አስተዳደርን፣ የጎርፍ አደጋ ስጋት ቅነሳና የተቋማትን የመረጃ ትንተና አቅም ለማሳደግ ሦስት ጥናቶችን አጥንቷል፡፡
ጥናቶቹ የሀይቁንና የተፋሰሱን መረጃ በመጠቀም የጎርፍ አደጋ ስጋት ቦታዎችን በመለየት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለማዘጋጀት የሚያግዙ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም የውሃ እና የአየር ሁኔታ መረጃዎችን በጥራት ለመያዝ የሚያስችል የቴክኒክና የተቋማት አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን ዩንቨርሲቲው በጥናቱ አመላክቷል።
ከዚህ ባሻገር በተቋማት መካከል ያለውን የቴክኒክ አቅም ክፍተት በመገምገም ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ አያያዝ መመሪያ መዘጋጀቱ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትና በሌሎች ተፋሰሶች (ዋቢሸበሌ እና ገናሌ ዳዋ) የአየር ንብረት መከታተያ ጣቢያዎችን መትከልና የቅድመ ማጠንቀቂያ ስርዓቶችን የመዘርጋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

