Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

102 ሚሊየን ብር ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች የገበታ ለሃገር የልማት ጥሪ በመቀበል 102 ሚሊየን ብር የሚሆን የአንድ ወር ደሞዛቸውን ድጋፍ አደረጉ፡፡

መንግሰት ከዚህ በፊት በገበታ ለሸገር ያቀረበውን የልማት ጥሪ በመቀበልና ፈጣን ምላሽ በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድነት ፓርክ፣ ሸገር የወንዝ ዳርቻ መናፈሻ፣ እንጦጦ ፓርክ ፍፁም በማይታመን መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ በከፍተኛ ርብርብ ውጤቱን ማየት ተችሏል ብሏል አገልግሎቱ፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ይህንኑ የልማት ስራ በማስፋት ወደ ሃገራዊ ትልም በማሳደግ ገበታ ለሃገር በሚል በቀጣይ 3 ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ነድፎ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪ እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮይሻ ለመተግበር የድጋፍ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው ፡፡

ተቋሙ የሚያደረገው ድጋፍ በገንዘብ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በአገልግሎትም የሚገለጽ በመሆኑ የአንድነት፣ የሸገር እና የእንጦጦ ፓርኮች ግንባታ ላይም የነበረው ሙያዊ አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

በቀጣይም በጎርጎራ፣ በወንጪ፣ በኮይሻና በሌሎች አከባቢዎች ለሚከናወኑ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዚያት እንዲጠናቀቁ የራሱን አስተዋጾ እንደሚያበርከት ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version