አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን አዘጋጅተው ሕዝብን በብቃት ማገልገል አለባቸው አሉ የአፍሪካ የአስተዳደር ማዕከል ሊቀመንበር ቤኔዲክታ ላሲ፡፡
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ቤኔዲክታ ላሲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ለመያዝ ከማቀድ ባለፈ ሀገራቸውን በብቃት ለመምራት፣ የረጅም ጊዜ የልማት አቅጣጫ ለመቅረጽና የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት መዘጋጀት አለባቸው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ተልዕኮ ሥልጣን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለሀገራቸው የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን አዘጋጅተው ሕዝብን በብቃት ማገልገል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ፓርቲዎች መሪዎችን ከማፍራት ባለፈ የመንግሥት አስተዳደርን፣ የሀገር ኢኮኖሚንና የተለያዩ የልማት ዘርፎችን ለመምራት የሚያስችሉ ዕውቀትና አቅም በቅድሚያ ሊገነቡ ይገባል ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ተቋማት ለመሪዎች የሚሰጡት የአራትና የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ቢኖርም የኢንዱስትሪ መሠረትን መገንባት፣ የኃይል ሥርዓትን ማስፋፋትና የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የረጅም ጊዜ ተከታታይ ሥራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
በፖለቲካዊ ሽግግር ምክንያት ቀጣይነት ያላቸው የልማት ሥራዎች መቋረጣቸውም ለሀገራት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የልማት ጉዞም በምሳሌነት አንስተተው፤ በተለያዩ ጊዜያት ወደ አዲስ አበባ በተመላለሱባቸው አጋጣሚዎች ከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስትለወጥ በተግባር መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት፣ በኃይል፣ በኢንዱስትሪና በምርታማነት የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እያደረገች መሆኗን ጠቁመው፤ በፈረንጆቹ 2024/25 በጀት ዓመት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገት 9 ነጥብ 2 በመቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸውን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀገሪቱን ለመለወጥ የተያዘውን ርዕይ በመደገፋቸው አመስግነዋል።
በአፍሪካ የልማት ፋይናንስ ፍላጎትና በሚገኘው ሀብት መካከል ያለውን ክፍተት ለመዝጋትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አህጉሪቱ በየዓመቱ ከ400 ቢሊየን ዶላር በላይ የልማት ፋይናንስ እጥረት እንዳለባት ጠቅሰው፤ በአንጻሩ ከ4 ትሪሊየን ዶላር በላይ ሀብት በአህጉሪቱ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ና የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ የሚዘልቁ ግቦች በመሆናቸው፤ በሥልጣን ላይ ያሉም ሆኑ በተቃዋሚነት የሚገኙ ፓርቲዎች የአህጉራዊ ቃል ኪዳኖችን ማወቅና ተግባራዊነታቸውን መደገፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በጉባኤው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ልምድ እንዲለዋወጡ፣ በጋራ እንዲማሩና አህጉሪቱን ወደ ተሻለ የዕድገት መንገድ ለማሸጋገር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ

