Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌትና የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሁሉ የነጻነት፣ የኩራት፣ የአሸናፊነት እንዲሁም የአንድነት ተምሳሌት ናት።

በውጪ ግንኙነቷ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅ የመገንባት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሁም አብሮ የማደግ መርህን ያካተተ አካሄድን ትከተላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የማደግን እንዲሁም አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግር መርህን የምትከተል ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር አህጉር ብቻ አትጋራም ይልቁንም የባሕል፣ የአኗኗር፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንም ይጨምራል፡፡

በዓድዋ ተራሮች ድል አድርጋ የነጻነት ተምሳሌት ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያን ምሳሌ አድርገው ማሸነፍ እንደሚቻል ተረድተው በርካታ ሀገራት ነጻነታቸውን አግኝተዋል፡፡

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መመስረት ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበረች፤ እነዚህና ሌሎች የተጽዕኖ ፈጣሪነት መልኮቿ ተደምረው የህብረቱ መቀመጫ በአዲስ አበባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ የሚመራው የቡርኪናፋሶ መንግሥት ኢትዮጵያ የነጭ ወራሪን አሳፍራ የመለሰችበትን ለሌሎችም ተምሳሌት የሆነችበትን ታላቁ የዓድዋ ድልን በሀገሪቱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተትና የመላው አፍሪካውያን የነጻነት፣ የጀግንነትና የአንድነት ማሳያ ተደርጎ ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን በመደገፍ እንዲሁም ምሳሌ ሆና በማሳየት ትታወቃለች፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የታሪክና የጂኦ ፖለቲካ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬም የዲፕሎማሲ ተሳትፎዋን በማሳደግ የአፍሪካዊ መፍትሄ አፍሪካዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፊት ተሰልፋ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ ባሻገር የተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት ለአፍሪካውያን ድምጽ እየሆነች ነው፡፡
በዚህም ተሳትፎዋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32ን እንድታዘጋጅ እድሉን አግኝታለች፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ እንዲሁም በቀጣናው ሰላምን በማስፈንና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ንቁ ተሳትፎን ታደርጋለች፡፡

ሰላም በሌለበት ልማት የሚታሰብ ባለመሆኑ የጋራ ጸጥታና ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ በትጋት ትሰራለች፡፡

በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ በመርህ ላይ የተመሰረተና ሌሎች የአካባቢውን ተጠቃሚ ያደረገ መንገድ መከተሏ ስጋትን ወደ ጋራ ልማት የመቀየር አካሄድ እንዳላት ያንፀባርቃል፡፡

የብሪክስ ህብረት አባል በመሆኗ ኢትዮጵያ ጂኦስትራቴጂያዊ ሚዛኗን ከማሳደጉ ባሻገር ድምጿን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማሰማትና በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ ዘርፎች ያላትን ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት ትልቅ ስትራቴጂያዊ ስኬት ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ወሳኝ ጥምረቶችን እያደረገች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዓማኒነቷን እየገነባችና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን እያሳደገች ትገኛለች፡፡

ይህም ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ተሳትፎ አዎንታዊ ውጤቶችን እያስገኘ ያለ የረጅም ጊዜ ርዕይ ውጤት ነው፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በቤተልሔም ግርማ

Exit mobile version