Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመቐለ ከተማ ለሕገ ወጡ ሕወሓት የምግብና ሎጂስቲክ ድጋፍ ሊሰጡ የተዘጋጁ ፍጆታዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቐለ ከተማ ሃውልቲ ክፍለ ከተማ ለሕገወጡ ሕወሓት የምግብና የሎጂስቲክ ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተው የነበሩ የተለያዩ ፍጆታዎች በሕብረተሰቡ ጥቆማና ከፀጥታ አካላት ጋር በተደረገ የጋራ ፍተሻ መያዛቸው ተገለጸ።
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል ለወታደራዊ ዓላማ የሚውሉ የኮንጎ ጫማዎችና ድርቆሽ እንጀራ እንዲሁም ፉርኖ ዱቄት፣ ዘይት፣ ጤፍ፣ በርበሬ፣ ሽሮና ሳሙና ይገኙበታል።
የተያዙት ፍጆታዎች በገንዘብ ሲገመቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ሲሆን፤ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ለአቅመ ደካሞች እንዲከፋፈሉ አድርጓል።
የመቐለ ከተማ ከንቲባ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪና የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሙላው አብርሃሌ እንዳሉት፤ የተያዙት ፍጆታዎች ለአቅመ ደካሞች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል።
በቀጣይም የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን በመመልከት ጥቆማ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በግዛቸው ግርማዬ
Exit mobile version