Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የውሃ ጸጋችንን አሟጠን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን እውን ለማድረግ እንሰራለን – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃ ጸጋችንን አሟጠን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን እውን ለማድረግ እንሰራለን አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ያዘጋጀው የ2019 በጀት ዓመት ክልላዊ የመስኖ ንቅናቄ መድረክ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ይገኛል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚሁ በወቅት እንዳሉት፤ ግብርናው በዝናብ ላይ ብቻ ከተመሰረተ የተለምዶ አሠራር በመውጣት ወደ መስኖ ልማት መሸጋገር የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ የሚለውጥ ብቸኛ አማራጭ ነው።
ክልሉ ያለውን እምቅ የውሃና የተፈጥሮ ጸጋዎች አሟጦ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ማወጅ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህም ስኬት የተጀመሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች “በጊዜ የለንም” መንፈስ በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አርሶ አደሩ ከመደበኛ ሰብል በተጨማሪ ከፍተኛ የገበያ ዋጋ ያላቸውን የሆርቲካልቸር ምርቶችን በመስኖ በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የምርትና ምርታማነት እድገትን ለማፋጠን የክላስተር ግብርና እና ዘመናዊ ሜካናይዜሽን ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በትራክተሮች እና በኮምባይነሮች የታገዘ ዘመናዊ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት የሰው ኃይልንና ጊዜን በእጅጉ እንደሚቆጥብ ጠቁመው፤ ከምርት ስብሰባ በኋላ የሚባክነውን ምርትም እንደሚያስቀር አስረድተዋል፡፡
ምርትን በጥሬው ከመሸጥ ወጥቶ እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህም በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ በርካታ ሥራ አጥ የሆኑ ለክልሉ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በመለሰ ታደለ
Exit mobile version