Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብልጽግና ፓርቲ እና ዛኑ ፒኤፍ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ እና የዚምባብዌ አፍሪካ ብሔራዊ ኅብረት አርበኞች ግንባር (ዛኑ ፒኤፍ) የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ዘላቂ ተቋማዊ ትስስርን፣ የልምድ ልውውጥንና ትብብርን የሚያስቀጥል ማዕቀፍ የያዘ ሲሆን፣ በአስተዳደር፣ በአመራር ልማት፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ እና በሀገራዊ ልማት ዘርፎች የጋራ ትብብርን ያካትታል።
የስምምነቱ መፈረም ሁለቱ ፓርቲዎች ለረጅም ጊዜ የቆየውን የፖለቲካ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ዘላቂ ትብብርን የሚያስቀጥሉ የተደራጁ አሠራሮችን ለመዘርጋት እያደረጉ ያሉትን ተከታታይ ጥረት የሚያሳይ ነው።
ይህም ተቋማዊ ትስስራቸውን የበለጠ ለማጠናከር፣ በጋራ ተሞክሮዎች ለመማማርና የየሀገራቸውን የልማት አጀንዳዎች ለማሳካት የሚያግዙ የጋራ ፍላጎት ያላቸውን የትብብር መስኮች ለመለየት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል።
ስምምነቱ በአዲስ አበባ 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (APPS 2026) በተሳካ ሁኔታ በተካሄደበት ወቅት መፈረሙም ልዩ ያደርገዋል።
ጉባኤው ለፖለቲካዊ ውይይት፣ ለግንኙነት መስፋፋት እና አዳዲስ የሁለትዮሽና የብዙወገን አጋርነቶችን ለመመሥረት አስፈላጊ አህጉራዊ መድረክ ፈጥሯል።
በጉባኤው ወቅትና ከጉባኤው ጋር በተያያዘ ከተከናወኑ ሌሎች ግንኙነቶች ጋር የተፈረመው ይህ ስምምነት፣ ዘላቂ የፖለቲካ ውይይት የጋራ ፍላጎቶችን ወደ ተቋማዊ ትብብር በመቀየር ያለውን ተግባራዊ ፋይዳ ያሳያል።
እነዚህ ክንውኖች የአፍሪካ ፖለቲካ ፖርቲዎች ዋነኛ ዓላማንም የበለጠ ያጠናክራሉ።
ይህም የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ውድድር ላይ ብቻ ከሚያተኩሩ ድርጅቶች ባሻገር፣ ለፖሊሲ ፈጠራ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለአመራር ልማትና ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ ዘላቂ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ጠንካራና ዘላቂ ተቋማት እንዲሆኑ ማበረታታት ነው።
ያሉ አጋርነቶችን ማጠናከር፣ አዳዲስ የትብብር ድልድዮችን መገንባት፣ ለአፍሪካ ልማትና ብልጽግና የጋራ ራዕይን ያሳድጋል።
Exit mobile version