Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተፈጥሮ ፈተናዎችን የመሻገር ጥበብ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤፍ ሲ) ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜያት በተፈጥሮ አደጋዎች ተፈትና ታውቃለች፤ ይህም ለኢኮኖሚዋ ከባድ ተግዳሮት ሲሆንባት ቆይቷል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይህ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመቋቋም እንዲሁም የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በማለም የተደረገ ነው፡፡
ዋነኛ መነሻው ሙሉ ለሙሉ በዝናብ ላይ ከተደገፈ የግብርና ሥርዓት ለመውጣት የተጀመረው የበጋ መስኖ ልማት ይህንን በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰት የምርት ችግርን ለመቅረፍ የሚተገበር አንዱ ስልት ነው፡፡
ይህም የሀገሪቱ ምርታማነት በዝናብ ላይ ብቻ የተመረኮዘ እንዳይሆን በማለም የተተገበረ በመሆኑ የድርቅ ችግርን ከመፍታት ባሻገር ምርታማነትንም ያሳድጋል፡፡
በበጋ ወራት ብቻ ሳይሆን በክረምት ወቅትም የዝናብ እጥረት ሊከሰት ይችላል፤ በዚህም ወቅት የመስኖ ልማት ዝርጋታዎች ይህንን ችግር የሚታደጉ ይሆናል፡፡
ሌላው ደግሞ በአረንጓንዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች ይተከላሉ፤ ይህም መሬት የማለምለም፣ እርጥበትን የመጠበቅ እንዲሁም የአፈር መሸርሸርን የመከላከልና የከርሰ ምድር ውሃን የመተካት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
በመሆኑም ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት እንኳን መሬቱ ምርታማነቱን እንዲቀጥል አስተዋፅኦ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚውም ዋስትና የሚሰጥ ተግባር ስለመሆኑም ይታመናል፡፡
ተፈጥሮ ዝናብን በምትከለክልባቸው ወቅቶች ደግሞ ዘመናዊና በሀገር ውስጥ የበለጸጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያ ደመና ማበልጸግ የጀመረች ሲሆን፤ ይህም የዝናብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ዝናብ እንዲጥል በማድረግ ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባሻገር በቴክኖሎጂ አደጋን የመከላከል ርምጃ ነው፡፡
የአየር ንብረት መዛባት ሲኖር አርሶ አደሩ እንደ ሜትሮሎጂ ካሉ ተቋማት መረጃዎችን አስቀድሞ ማግኘት እንዲችል ሆኗል፡፡
የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲቀነባበሩ እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ውጪ እንዲላኩ መደረጉ ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ መዋዥቅና ከምርት እጥረት እንድትጠበቅ ያደርጋል።
በከተሞች የሚፈጠረው የኢንዱስትሪ ስራ እድል በገጠር አደጋ በሚከሰትበት ወቅት የቤተሰብ ገቢን የሚደግፍና የኢኮኖሚ ጫናን የሚያቃልል አማራጭ በመሆን ያገለግላል።
በተጨማሪም አደጋዎች ከተከሰቱም በኋላ አርሶአደሩ በፍጥነት ማንሰራራትና ዳግም እንዲመለስ የሚያስችሉ የፋይናንስ ስርዓት ዝርጋታ ነው፤ አነስተኛ የብድርና የፋይናንስ አቅርቦቶች መኖራቸው መልሰው ወደ ምርት እንዲገቡ አቅም ይሆናቸዋል፡፡
በዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ሥጋት የነበረ ቢሆንም በመንግሥትና በሕዝብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መልካም የሚባል አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራች በመሆኑ ለግብርናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦን እያበረከተ ይገኛል፡፡
በቤተልሔም ግርማ
Exit mobile version