Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የአዲስ አበባ ቃልኪዳንን በማፅደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ የአዲስ አበባ ቃልኪዳንን (Addis Ababa Declaration) በማፅደቅ እና የጋራ መግለጫ በማውጣት በዛሬው ዕለት በስኬት ተጠናቅቋል።

ጉባኤውን ያጠናቀቁት የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች አህጉሪቱን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ከፍታ ለማሻገር የገቡትን ቃል የሚያረጋግጥ ባለ 22 ነጥብ የአዲስ አበባውን መግለጫ አፅድቀዋል።

በመግለጫው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር የፖለቲካ አመራሩ ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን ፓርቲዎቹ አረጋግጠዋል።

አህጉሪቱ ከተፈጥሮ ሀብት ጥሬ ዕቃ ላኪነት ወጥታ በሀገር ውስጥ ምርት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ላይ እንድታተኩር በጋራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

ማንኛውንም ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ የመንግሥት ስልጣን ለውጥን ፓርቲዎቹ ያወገዙ ሲሆን በዲሞክራሲያዊ ተጠያቂነት እና በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አድሰዋል።

ሴቶች በፖለቲካ አመራር እና በኢኮኖሚ ውሳኔ ሰጪነት ላይ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በመስማማት በአህጉሪቱ ያለውን የወጣቶችን አቅም ለመጠቀም በትምህርት እና በሥራ ፈጠራ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ከአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ጋር የሚጣጣም እና የአፍሪካን የፖለቲካ ፓርቲዎች የወደፊት የጋራ ራዕይ የሚወስን “APPI Agenda 2040” የተሰኘ አዲስ ስትራቴጂያዊ ቻርተር ለማዘጋጀት አህጉራዊ ምክክር ለመጀመርም ተወስኗል።

ይህ አዲሱ ስትራቴጂያዊ ቻርተር በይፋ የፀደቀ ሲሆን የአመራር ቢሮ ተቋቁሟል።

በኢትዮጵያ የሚገኘውን የለውጥ አመራር የፖለቲካ አካዳሚን ጨምሮ የአፍሪካ የፖለቲካ ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ተስማምተዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለብልጽግና ፓርቲ ላደረጉት የላቀ መስተንግዶ እና ላሳዩት አጋርነት አመስግነዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

Exit mobile version