ጉባኤው አፍሪካ የጋራ ዕጣ ፈንታዋን በራሷ ለመወሰን ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው – ብልፅግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አፍሪካ የጋራ ዕጣ ፈንታዋን በራሷ አቅም ለመወሰን ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው አሉ ብልፅግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል።
ላለፉት ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በታላቅ ስኬት ተጠናቅቋል።
ጉባኤውን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት አቶ ነብዩ ስሁል፤ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተለያዩ ልዑካን፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በተገኙበት ተካሂዶ በስኬት መተናቀቁን ገልጸዋል።
ጉባኤው ከተለመደው የአዳራሽ ውይይት የዘለለ እና የኢትዮጵያን ተጨባጭ የልማት ሥራ አፍሪካውያን በአካል የተመለከቱበት አኩሪ መድረክ ነው ብለዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በቆይታቸው ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ውብ ያደረጉ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የሰው አቅም፣ ቴክኖሎጂ እና የሐሳብ ጥራት የተዋሃዱባቸውን የመሶብ አገልግሎቶች መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የኢትዮጵያ የልማት ማሳያዎች እንደ አዲስ ብራንድ ተሞክሮ ተወስደው ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት እንዲስፋፉ ሰፊ መድረክ መፈጠሩን አስረድተዋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር ያስቻሉ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ‘የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ’ መሪነት በብልፅግና ፓርቲ እንዲመራ ተወስኖ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ ዋና ጸሐፊ በመሆን መመረጣቸውን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያነሷቸው አዳዲስ አህጉራዊ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ተካተው ‘የአዲስ አበባ ቃልኪዳን’ በይፋ መጽደቁን ጠቁመዋል።
አቶ ነብዩ ስሁል በመግለጫቸው ይህ ቃልኪዳን የፖለቲካ አመራር ከባህላዊው አሰራር ወጥቶ በቀጥታ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲችል አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አብራርተዋል።
አዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ወደ አመራርነት እንዲመጣ የሚጠይቀውን ቁልፍ አጀንዳ በጋራ ቃልኪዳናቸው አፍሪካውያን ሰንደዋል ያሉት አቶ ነብዩ ጉባኤው አፍሪካ የጋራ ዕጣ ፈንታዋን በራሷ አቅም ለመወሰን ያላትን ቁርጠኝነት ባረጋገጠ መልኩ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ መጠናቀቁን በመግለጫቸው አስረድተዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በዓለምሰገድ አሳዬ

