አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች የምታንፀባርቅበት እና የቀጣይ አዘጋጅ ኃላፊነቷን የምትረከብበት 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በነገው ዕለት በቱርክ መካሄድ ይጀምራል፡፡
በቱርክ አንታሊያ ከተማ የሚደረገው ጉባኤ ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር(“Where dialogue turns into global action”) በሚል መሪ ቃል ከነገ ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ ህዳር 20 ይካሄዳል፡፡
የአየር ንብረት ፋይናንስ፣የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሂደት፣ፍትሃዊ የኃይል ሽግግር እና የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያስከትላቸው ጉዳቶች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰብ በጉባኤው ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች መሆነናቸው ተመላክቷል፡፡
የምግብ ብክነትን እና የሚቴን ጋዝ ልቀትን መቀነስ፣የንፁህ ኢነርጂ ሽግግር፣የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ ከተሞችን መገንባት፣አረንጓዴ ኢንዱስትሪ፣የምግብ ዋስትና እና ደህንነት፣የባህር ውስጥ ስነ-ምህዳር ጥበቃ እና ጤናማ የአየር ንብረት ስርዓት የጉባኤው ንዑስ አጅንዳዎች ናቸው፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ የምትሳተፍ ሲሆን በጉባኤው የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች የምታንፀባርቅ ሲሆን የአህጉሪቱን ልዩ የአየር ንብረት ተጋላጭነት እና ፍላጎቶች ለዓለም ታስተዋውቃለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ያከናወነቻቸውን የአረንጓዴ ዐሻራ እና ሌሎች አረንጓዴ የልማት ሥራዎችን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታሳይበት መድረክም ነው፡፡
በጉባኤው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ፣የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማፋጠን እንዲሁም የአቅም ግንባታ እና ክህሎት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደምትመክርም ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም የቱሪዝም እና የማዕድን ልማትንለማሳደግ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር፣የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ማነቃቃት እና ዘላቂ የማዕድን ልማት ጉዳዮችን በተመለከተ በአጀንዳነት ታነሳለች፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ ይህን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መድረክን ለመምራት እንዲሁም ለጉባኤው የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ሎጅስቲክስ ፣የጸጥታና የትራንስፖርት ዝግጅቶችን ለማከናወን የሚያስችል ልምድ ከመድረኩ ትቀስማለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ

