አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ረገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች።
በዚህ ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ የሆነ ከባቢን ለማስረከብ የምታደርገውን ጥረት በግልጽ ያሳያል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ ከመቼውም ጊዜ በላይ የደን ሽፋንን በማሳደግ በካይ ጋዝን በመቀነስ ረገድ የላቀ ሚና ተጫውቷል።
የተከሉት በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የነጠፉ መሬቶችን በማከም፣ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲያገግም፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቆምና ብዝሃ-ሕይወት ዳግም እንዲያንሰራራ አድርገዋል።
ይህ ተሞክሮ ለጎረቤት ሀገራት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የችግኝ ስጦታዎችንና የእውቀት ልውውጦችን በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል ትልቅ ሞዴል ሆኗል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቆጣጠር ንጹህና ዘላቂ ልማትን እያረጋገጠች ነው።
የኃይል አቅርቦቷ ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ምንጮች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ንጹህ ኃይልን ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት ማዳረስ ተችሏል።
በተጨማሪም መንግሥት ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከጉምሩክ ቀረጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረጉ የነዳጅ ጥገኝነትንና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የከተሞችን አየር ንጽህና እየጠበቀ ይገኛል።
ይህንን አረንጓዴ እና ዘላቂ የልማት ጉዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የአፍሪካን ድምጽ ለማሰማት ኢትዮጵያ በቱርክ አንታሊያ ከተማ በሚካሄደው 31ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ላይ በንቃት እየተሳተፈች ይገኛል።
በዚህ ትልቅ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ልዩ የአየር ንብረት ተጋላጭነት እና ፍላጎቶች ለዓለም በማስተዋወቅ የአህጉሪቱን ድምጽ ታሰማለች።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን ኮፕ 32 ዓለም አቀፍ መድረክ ለማዘጋጀት የተመረጠች ሀገር እንደ መሆኗ መጠን፤ ከዚህ ጉባኤ የኮፕ አስተናጋጅነት ልምዶችን፣ ዓለም አቀፍ ሎጅስቲክስን፣ የጸጥታና የትራንስፖርት ዝግጅቶችን አፈጻጸም በመቅሰም ቀጣዩ ታሪካዊ ኃላፊነቷን ትረከባለች።
አጠቃላይ የኢትዮጵያ የተቀናጀ የልማት ጉዞ የደን ልማትን ከዘላቂ የግብርና ሥርዓት እና ከንጹህ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀቱ ለአሁኑ ትውልድ የኢኮኖሚ እፎይታን ከመስጠት ባለፈ ዓለምን እየታደገ ያለ እና ለአህጉሪቱም ምሳሌ የሆነ ዘላቂ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

