Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ለአፍሪካ አርዓያ እየሆነች ያለችው ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ማስማማት የግድ ሆኗል።
ይህንን ተጽእኖ ለመቋቋም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫዋ ጋር በማቀናጀት ወደ በተግበር ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ የዛሬ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልዶች የተሻለች፣ የተፈጥሮ ሀብቷን የጠበቀችና በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገር የመገንባት ራዕይ ነው።
በዚህም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ የከተሞች አረንጓዴ ውበትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሀገሪቱ የአረንጓዴ ልማት አካል ሆነዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ የታየበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የተራቆቱ መሬቶችን ለመመለስ፣ የውሃና የአፈር ጥበቃን ለማጠናከር እንዲሁም የሥነ ምህዳር ሚዛንን ለመጠበቅ የተከናወነው ስራ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
መርሐ ግብሩ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የዜጎችን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በማሳደግና የጋራ ኃላፊነትን በማጠናከር ረገድም የራሱን ዐሻራ እያሳረፈ ይገኛል።
ከዚህ አኳያ የአረንጓዴ ዐሻራ ስራ ለአሁኑ ትውልድ የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ የተሻለ የኑሮ መሠረት የሚጥል ሀገራዊ እንቅስቃሴ ሆኗል።
በተመሳሳይ የታዳሽ ኃይል ልማት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ ነው።
ሀገሪቱ ያላትን የውሃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል ኃይል አቅም ወደ ልማት በመቀየር የኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ ባለፈ ከብክለት ነፃ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ እየሰራች ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የታዳሽ ኃይል አቅም ከፍ በማድረግ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር የጎላ ሚና አለው፡፡
በግብርናው ዘርፍም የአረንጓዴ ልማት አስተሳሰብን ወደ ተግባር የማሸጋገር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የአፈር ለምነትን መጠበቅ፣ የውሃ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የሰብል ምርታማነትን ማሳደግና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ የምርት ዘዴዎችን ማስፋፋት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚያስተሳስሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ጥረቷ በአህጉሪቱ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ውስጥ ያላትን ሚና በማሳደግ ለአፍሪካ የጋራ ጥቅም የሚበጁ መፍትሄዎችን ለማፍለቅ እየሰራች ትገኛለች።
ለአብነትም በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የአህጉሪቱን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ክስተት ነው።
በነገው ዕለት በቱርክ መካሄድ በሚጀመረው የኮፕ-31 ጉባኤ የኢትዮጵያ ኃላፊነት የአረንጓዴ ልማት ልምዷን ለዓለም ከማቅረብ ባለፈ ይህንን አህጉራዊ ድምጽ ታስተጋባለች፡፡
ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ተጨባጭ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-32) ለማስተናገድ መመረጧ የሚታወስ ነው፡፡
ይህ ዲፕሎማሲያዊ ድል የሀገሪቱን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ይበልጥ ለማፋጠን የሚያስችል ታሪካዊ እድል ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ
Exit mobile version