Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአንታሊያ እስከ አዲስ አበባ – ስለ ምድራችን የሚመከርበት ታላቅ ሁነት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ዓለም በየዓመቱ በአንድ ጣራ ስር ተሰብስባ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ ከምትመክርባቸው ጉዳዮች መካከል የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ) ቀዳሚው ነው፡፡
ይህ ታላቅ ሁነት የአንዲት ሀገር ብቻ ሳይሆን የመላው የዓለም ሕዝብና የምድራችን እጣ ፈንታ ነው።
‎በነገው ዕለት የ31ኛው ምዕራፍ መጋረጃ በቱርክዬ የባህር ዳርቻ ከተማ አንታሊያ ይከፈታል፤ ጉባኤው እስከ ህዳር 20 ይቀጥላል።
ወደ 200 የሚጠጉ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በአንታሊያ ኤክስፖ ማዕከል ይገናኛሉ።
‎
‎በኮፕ አደባባይ ምን ይሆናል?
‎
‎ኮፕ አንድ አዳራሽ፣ አንድ ንግግር አይደለም፤ ብዙ መድረኮች የተሳሰሩበት የሃሳብ ገበያ ነው።
‎
‎የመጀመሪያው የድርድር አዳራሽ ነው፤ የሀገራት ተደራዳሪዎች ቃል በቃል፤ አንቀጽ በአንቀጽ ይከራከራሉ።
የሚወጣው ውሳኔ በሁሉም ሀገራት ስምምነት መጽደቅ ስላለበት እስከ ሌሊት፤ አልፎም እስከ ንጋት የሚዘልቁ ድርድሮች የተለመዱ ናቸው።
‎
‎ሌላኛው ደግሞ የመሪዎች ጉባኤ ነው፤ በመጪው ህዳር 11 እና 12 የሀገር መሪዎች በአንታሊያ ተሰባስበው ሀገራዊ ቁርጠኝነታቸውን ያቀርባሉ፤ ጎን ለጎንም ሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ።
‎
‎ሦስተኛው የድርጊት አጀንዳ ነው፤ ከመንግስታት ባሻገር ከተሞች፣ ኩባንያዎች፣ ባለሀብቶችና ማህበረሰቦች ተግባራዊ መፍትሄዎችን ይዘው ይመጣሉ።
‎
‎4ኛው ሁነት፡ ዳር ያለው ሕያው ገበያ ነው፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጎንዮሽ ውይይቶች፣ የሀገራት ድንኳኖች፣ የወጣቶችና የሲቪል ማህበራት ድምጽ፣ የሀገር በቀል ማህበረሰቦች ጥሪ፣ ሁሉም በአንድ ቦታ ይሰማሉ።
ብዙ ጊዜ ዋነኛው ዜና ከዋናው አዳራሽ ሳይሆን ከእነዚህ ኮሪደሮች ይወለዳል።
‎
‎ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?
‎
‎የመጀመሪያ ጉዳይ አመራር ሞዴል ነው፤ በኮፕ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉባኤው ኃላፊነት በሁለት ሀገራት ተከፍሏል።
ቱርክ አስተናጋጅና ፕሬዚዳንት ናት፤ የአካባቢ ሚኒስትሯ ሙራት ኩሩም ጉባኤውን ይመራሉ፤ የድርጊት አጀንዳውንም መምራትም የእሳቸው ስራ ይሆናል።
አውስትራሊያ ደግሞ “የድርድር ፕሬዚዳንት” የሚል ልዩ ሚና ይዛለች፤ ሚኒስትሯ ክሪስ ቦወን መደበኛውን ድርድር ይመራሉ።
‎
‎ይህ ዝግጅት ከረጅም ውዝግብ በኋላ የመጣ ድልድይ ነው። ሁለቱም ሀገራት አስተናጋጅ ለመሆን ተወዳድረው ነበር፤ በኮፕ 30 ማብቂያ ላይ ስምምነት ተደረሰ።
‎
‎የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አውስትራሊያ የፓስፊክ ደሴት ሀገራትን ድምጽ እንድታሰማ ዕድል የሚሰጥ ነው፤ ስለዚህ የመጀመሪያ ዝግጅት ስብሰባዎች በጥቅምት ወር ከፊጂና ቱቫሉ ጋር በፓስፊክ ተካሂደዋል።
ከፍ ያለ የባህር ጠለል ህልውናቸውን የሚፈትናቸው ሀገራት ድምጻቸው በዚህ ጉባኤ ሰፊ ቦታ አግኝቷል።
‎
‎ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው፤ የሚቀጥለው ጉባኤ (ኮፕ 32) በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
‎
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው ‎አዲስ አበባ ባለፈው ዓመት የሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በማስተናገድ ብቃቷን አሳይታለች።
አፍሪካ ከተጎጂነት ወደ መፍትሄ አቅራቢነት የምትሸጋገርበት ወሳኝ ምዕራፍ ከፊታችን ነው።
Exit mobile version