አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ዓለምን እያስጨነቀ በባበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ተፈጥሮን በመንከባከብ የአየር ንብረት ፋይናንስ ምንጮችን ለማብዛት የሚያስችል አዲስ ዕድል ፈጥራለች፤ እርሱም የካርቦን ሽያጭ ነው።
የካርቦን ሽያጭ ማለት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚለቀቁ፣ በተለይም እንደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያሉ በካይ ጋዞችን በመቀነስ ወይም በማስወገድ የተገኘውን የልቀት መጠን እንደ አንድ የንግድ ምርት በመቁጠር የመገበያያ ዘዴ ነው። የካርቦን ሽያጭ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ወደ ዘላቂ የገንዘብ ምንጭ በመቀየር ለአካባቢና ማህበረሰብ ልማት ሰፊ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በዓለም አቀፍ ደረጃ ደንን በመጠበቅ ኢትዮጵያ የካርቦን ሽያጭ ክፍያ ከሚያገኙ አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ በካርቦን ገበያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተቋማዊ አሠራርንና የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅታለች፤ በዚህም የካርቦን ገበያን የሚደነግግ አዋጅ ቁጥር 1436/2018 ሰኔ 2018 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቃለች። አዋጁ ሀገራችን በዓለም ካርቦን ገበያ እንድትሳተፍ እና ሙዓለ ነዋይ እንድትስብ የሚያግዝ ነው።
ሌላኛው የሕግ ማዕቀፍ በቀድሞው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የብሔራዊ የካርቦን ማዕቀፍ (2025–2035) ሲሆን፣ የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት መሠረት በማድረግ የካርቦን ሽያጩ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ነው።
በታኅሣሥ 2018 ይፋ የተደረገው የደን ካርቦን ንግድ መመሪያም ማኅበረሰቦች፣ ባለሃብቶችና ክልሎች በደን ልማት ያመረቱትን የካርቦን ክሬዲት በሕጋዊ መንገድ እንዲሸጡ የሚያስችል አሠራር የፈጠረ ነው።
በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥራት ላላቸው በተፈጥሮ ላይ የተመሠረቱ የካርቦን ክሬዲቶች ያለው ፍላጎት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ ለሀገሪቱ ትልቅ ዕድል ከፍቷል።
በኢትዮጵያ ዋነኛ የካርቦን ምንጮችና ዘርፎች ከሚባሉት ውስጥ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያሉ የደን ልማትና ጥበቃ ሥራዎች፣ የታዳሽ ኃይል ልማት እና በካይ አየር የማይለቅቁ ዘመናዊ የቤት ውስጥ ማብሰያ ምድጃዎችን መጠቀም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የካርቦን ገበያ የደን ጭፍጨፋን በመቀነስ፣ የተጎዱ መሬቶችን እንዲያገግሙ በማድረግ እና የከባቢ አየር ሙቀትን የሚጨምሩ በካይ ጋዝ ልቀቶችን በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና አለው።
ከ56 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከካርቦን ገበያ ጋር በመቀናጀቱ የተተከሉ ደኖች በሳይንሳዊ መንገድ ተለክተውና ተረጋግጠው ተጨማሪ ፋይናንስ የሚያስገኙበት መንገድ ተመቻችቷል።
ኢትዮጵያ በካርቦን ሽያጭ አማካኝነት ከዓለም ባንክ እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ባደረገቻቸው ስምምነቶች ከ70 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።
ከካርቦን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ማኅበረሰቡ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲወስድ በሕግ ጭምር መደንገጉን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም አስገንዝበዋል። በዚህም ማኅበረሰቡ ደንን በመጠበቁ ቀጥተኛ የገንዘብ ክፍያና አማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲያገኝ እንዲሁም የግብርና ምርታማነትን ከፍ እንዲል ያግዛል።
ኢትዮጵያ በካርቦን ሽያጭ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የተጠናከረ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ጉዳትን የመቀነስ ጥረቷ ለዓለም አብነት የሚሆን ነው።
በቴዎድሮስ ሳህለ

