አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታከናውናቸውን ተግባራት ለዓለም ለማሳየት ኮፕ – 31 ትልቅ እድል ይፈጥራል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኮፕ – 31 የተከፈተውን የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራችባቸው ያሉትን ዋና ዋና ግቦች ይፋ አድርገዋል።
በኮፕ – 31 የሚኖረው የድርድር ሂደት ውጤታማ ሆኖ ለኮፕ32 ስኬት ጠንካራ መሰረት እንዲጥል ማድረግ ዋነኛው ግብ እንደሆነ አንስተው፤ ይህንን ለማሳካት ከቱርኪዬ እና አውስትራሊያ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለኮፕ – 32 አጋር ከሚሆኑ የተለያዩ አካላት ጋር የጋራ መግባባት መፍጠር እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ዓላማዎችና ሀሳቦች ሰፊ ውይይት ማድረግ ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኮፕ – 32 ጉባኤን በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠብቅና በቁጥር ሰፊ የሆነ ታዳሚ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታከናውናቸውን ስራዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰፊው ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የሚፈጥር መድረክ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት አየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 31) ‘ከቃላት ባለፈ ወደ ተግባርና አፈጻጸም መሸጋገር’ በሚል መሪ ሀሳብ በቱርኪዬ አንታሊያ ከተማ በዛሬው ዕለት መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

