Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባ፤ ከአህጉራዊ ማዕከልነት እስከ ዓለም አቀፍ ስበት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነችው ከተማ አዲስ አበባ የሚደነቅና ፈጣን ለውጥ እያሳየች ትገኛለች።
የአዲስ አበባ ውበት በኮሪደር ልማቷና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶቿ፣ በዘመናዊነት በተገነቡ ሕንፃዎቿና በመናፈሻ ቦታዎቿ፣ ብቻ ሳይሆን በእንግዳ ተቀባይነቷም ጭምር ይለካል፡፡
በመዲናዋ ያለው ሰላምና ጸጥታ ጋር ከኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ጋር ተዳምሮ እንግዶች እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የትራንስፖርት አገልግሎቶች መሻሻል እና የሆቴል መሠረተ ልማቶች ዘመናዊ መሆን ለዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዶች የሚመጥን ምቹ አካባቢን ዘርግቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኮሚሽንና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል ነች፡፡ ይህና ሌሎች ምክንያቶችም ተደማምረው ለተለያዩ የአህጉርና ዓለምአቀፍ መድረኮች ማዘጋጃነት ተመራጭ አድርገዋታል፡፡
አዲስ አበባ ደረጃቸውን የጠበቁ የስብሰባ ማዕከላትና ሆቴሎች ባለቤት እንዲሁም የዲጂታል የመሰረተ ልማቶቿ የተሟሉላት ከተማ መሆኗ ለኮንፈረንሶች ተመራጭ ያደረጋት ሌላው መልክ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በመጠቀም ግንባር ተሳታፊ ናት፡፡
እንዲሁም ለሌሎች ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ተግባርን በመከወኗ እና ባደረገቻው በጎ ጥረቶች የተነሳ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32)ን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች፡፡
የተለያዩ ኮንፈረንሶች በከተማዋ መካሄዳቸው የከተማዋን የቱሪዝም አቅምና ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር ገጽታ በመገንባትና የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ እንግዶች እንዲረዱት በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ጉባኤ ለማካሄድ የሚመጡ እንግዶችም የስብሰባ ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ያልመጡትም የመምጣት ተነሳሽነት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ነው፡፡
በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተለይም የከተማ እድሳትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለስብሰባ ተሳታፊዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ፈጣንና ቀልጣፋ አድርጎታል።
አዲስ አበባ ስሟ ሲነሳ የሰላም፣ የውበት እና የእድገት ምልክት ሆና እንድትታይ የማድረጉ ሂደት አሁን ላይ ፍሬው እየታየ ከተማዋ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውይይቶች ዋና መድረክ በመሆን ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በመሆኑም ከተማዋ በተፈጥሮ ጸጋዋ ያገኘችው ውበት፣ ለኑሮና ለሥራ የተመቸ አቀማመጧ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ተደምረው የነገዋን አፍሪካዊ ብሩህ ተስፋ የሚያንጸባርቅ ታላቅ ከተማ አድርገዋታል።
በቤተልሔም ግርማ
Exit mobile version