Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮፕ 31፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮዋን ለዓለም የምታሳይበት መድረክ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማ ልማት መንገዶችን ከመገንባትና የከተማን ገጽታ ከማስዋብ አልፎ የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ፣ የአካባቢ ጥበቃን የሚያጠናክሩና ለዘላቂ ዕድገት መሠረት የሚጥሉ የተቀናጁ ሥራዎችን ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተማ ልማትን ከአረንጓዴ አካባቢ እንዲሁም ቅርስ ጥበቃ ጋር በማቀናጀት እየሰራች ትገኛለች።
ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን የመጓጓዣ አቅም ከማሳደግ ባለፈ የአካባቢ ጥበቃንና ለሕዝብ ምቹ የሆኑ የከተማ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ያለሙ ናቸው።
ሰፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች መካተታቸው የእግረኞችንና የብስክሌተኞችን ደኅንነት ከማሻሻል ባለፈ አማራጭ የትራንስፖርት አጠቃቀምን ያበረታታል።
የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማት የከተማዋን የተፈጥሮ ሀብት ለማሳደግ እንዲሁም የአየር ጥራትንና የአካባቢ ውበትን ለማሻሻል የሚያግዝ ሲሆን፤ የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ወንዞች ከብክለትና ከአካባቢ መበላሸት ለመታደግ የተያዘ ትልቅ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ነው።
እነዚህ ሥራዎች የወንዝ ዳርቻዎችን ከብክለትና ከተፈጥሮ አደጋ ስጋት በማላቀቅ ወደ አረንጓዴ መዝናኛ፣ ስፖርት፣ ቱሪዝምና ማኅበራዊ መስተጋብር ማዕከላት ለመቀየር የሚያስችሉ ናቸው።
በዚህም የከተማዋ የተፈጥሮ ሀብት ከመጠበቁ ባለፈ ለነዋሪዎች ጤናማና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ይፈጠራል።
እነዚህ የከተማ ልማት ተግባራት በአዲስ አበባ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጥበቃ መድረኮች ላይ ልምዷንና የልማት አቅጣጫዋን ለማስተዋወቅ ከምታደርገው ጥረት ጋርም ይያያዛሉ።
ሀገሪቱ የኮፕ – 32 አስተናጋጅ መሆኗ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር አዲስ ዕድል ከፍቷል።
ይህ ኃላፊነት ዓለም አቀፍ ጉባኤን ከማስተናገድ ባለፈ የአፍሪካን የአየር ንብረት ተግዳሮቶች፣ የመፍትሔ ሐሳቦችና የልማት ፍላጎቶች በዓለም አቀፍ ውይይት ውስጥ የበለጠ ቦታ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
በቱርኪዬ አንታሊያ ከኅዳር 9 እስከ 20 ቀን 2026 የሚካሄደው የኮፕ – 31 ጉባኤ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀውን ኮፕ32 ዝግጅት ለማጠናከር ወሳኝ የተሞክሮ ማግኛ መድረክ ነው።
በዚህ ጉባኤ ላይ የሚደረጉ ውይይቶችና የሚገኙ ግብዓቶች በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ በንጹህ ኃይል፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች የሀገሪቱን አቅም ለማሳደግ ያግዛሉ።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በደን ጥበቃ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዘርፎች የምታከናውናቸው ተግባራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ሊቀርቡ የሚችሉ ተጨባጭ ልምዶች ናቸው።
እነዚህ ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ከኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ከማኅበራዊ ተጠቃሚነት ጋር በማቀናጀት ሊከናወን እንደሚችል ያሳያሉ።
በተለይም አዲስ አበባ በወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ በከተማ አረንጓዴነት፣ በዘመናዊ ትራንስፖርትና በሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ የምታከናውናቸው ሥራዎች ለዘላቂ የከተማ ልማት ተግባራዊ ምሳሌዎች ናቸው።
የኮፕ32 ዝግጅት ኢትዮጵያ ያላትን የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ ለዓለም ከማቅረብ ባለፈ ከሌሎች ሀገራት ልምድ ለመቅሰም፣ የጋራ መፍትሔዎችን ለማፍለቅና የአየር ንብረት ለውጥን በትብብር ለመቋቋም የሚያስችል አስፈላጊ ዕድል ነው።
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version