አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በተፈጥሮ ሀብት ለታደሉ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
በዚህም ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል አቅርቦት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት የአፍሪካ የኃይል ማማ ለመሆን በቅታለች፡፡
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፤ ከእነዚህም መካከል አብዛኛው በገጠሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የአኗኗር ዘይቤ በእንጨትና በማገዶ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
የታዳሽ ኃይል አቅርቦት መስፋፋት ግን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ለሌለባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን ለማዳረስ ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የንፋስ፣ የውሃ፣ የጸሐይና የጂኦተርማል ኃይሎችን በመጠቀም በነዳጅና በከሰል ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ትገኛለች።
የንፋስ ኃይል ልማቷን በአሸጎዳ ፕሮጀክት ግንባታ የጀመረች ሲሆን በአዳማ 1 እና 2፣ በአይሻ 1 እና በአሰላ ፕሮጀክቶች አስቀጥላለች።
የንፋስ ኃይል ማመንጫ የንፋስን ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር ለአገልግሎት የሚያውል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ከእነዚህም መካከል እንደ አብነት የሚጠቀሰው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያ ንጹሕና አስተማማኝ ኃይል የመጠቀምና በኃይል ራስን የመቻል ጉዞዋን ያጠናክራል፡፡
ይህ የአሰላ ኃይል ማመንጫ ቢበዛ በሁለት ዓመት ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ትርፋማ ስለሚሆን ልጆቻችን ትርፍ ሀብት የሚያገኙ እንጂ ዕዳ የሚረከቡ አይሆኑም በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ፓርኮችና ለፋብሪካዎች መስፋፋት በቂ የኃይል አቅርቦት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤ ፕሮጀክቱ አቅም በመፍጠርና የሥራ ዕድል በማስፋፋት ረገድ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
የነዳጅ ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት የማይገመትና ሽቅብ የሚወጣ ከመሆኑ ባሻገር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ከምታደርገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ መሆኗ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮላታል፡፡
ፕሮጀክቱ ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና ለጎረቤት ሀገራት ኃይል ለመሸጥ በማስቻሉ፣ ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል የማድረግና የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚናዋን የማሳደግ አቅም አለው፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም የአኗኗር ዘይቤንና ኢኮኖሚን ለማሻሻል፣ ጥገኝነትንም ለመቀነስ እያደረገችው ያለችው ጥረት ለሌሎች ሀገራትም ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ነው፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በቤተልሔም ግርማ

