አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ አባል ሀገራት ጋር ያላት ሁለንተናዊ ትብብር እና የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ አባል ሀገራት የተወጣጡ 16 የሚዲያ ተቋማት የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን የጋራ መድረክ በቻይና ቤጂንግ እየተካሄደ ነው።
መድረኩ ቻይና በኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አሁን ላይ የደረሰችበትን የልህቀት ደረጃና ተሞክሮ ለአባል ሀገራቱ ለማካፈል ያለመ ነው።
በመርሐ ግብሩ የቻይና ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘመኑን የዋጀ የሚዲያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተፅዕኖ ፈጣሪ የይዘት ሥራዎችን ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) እና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዕለት ተዕለት የይዘት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን አብራርተዋል።
የቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ፕሬዚዳንት ዝሁ ያናን፣ መገናኛ ብዙኃን የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ሚዲያ ተደራሽነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፥ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መረጃዎች የሀገራቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር የሚያጠናክሩ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ቻይና ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ አባል ሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ እየተሳተፉ የሚገኙት የተለያዩ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን ተወካዮች በበኩላቸው፥ በቻይና ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚዲያ ተቋማት እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።
ከቻይና የተወሰዱ ተሞክሮዎች በቀጣይ ለሀገራቸው የሚዲያ ተቋማት ዕድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎች በጋንዙ ቲያንጂ ግዛት የሚገኘውን የጋንዙ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጨምሮ ታሪካዊውን ታላቁ የቻይና ግንብ ጎብኝተዋል።
የቻይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያ የሆኑት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ማዕከላትም በሚዲያ ባለሙያዎች ከተጎበኙት መካከል ይጠቀሳሉ።
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ቻይና በፈረንጆቹ 2013 የጀመረችው ዓለም አቀፍ የመሠረተ ልማት እና የንግድ ትስስር ስትራቴጂ ነው።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ቻይናን ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከሌሎች የእስያ ሀገራት ጋር በየብስ እና በባሕር መስመሮች ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዚህ ፕሮጀክት ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እና ሞዴል ሀገር ተደርጋ ትወሰዳለች።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ በመድረኩ እየተሳተፈ ይገኛል።
የጋራ መድረኩን የቻይና ብሮድካስቲንግ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ቴክኒካል ትብብር ኩባንያ ከቻይና ንግድ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
በበኃይሉ ጌታቸው

