አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግል የሀገራትን የጋራ ትብብር፣ ተከታታይ ውይይትና ተግባራዊ ርምጃ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የ32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ- 32) አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ፤ ለጉባኤው ስኬታማነት ከወዲሁ የተቀናጀ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በተለይም በኮፕ-31 ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ለቀጣዩ ጉባኤ መሠረት በመጣል ኢትዮጵያ የአስተናጋጅነት ኃላፊነቷን በተቀናጀ መንገድ እንድትወጣ የሚያግዝ ወሳኝ አጋጣሚ ነው።
ኢትዮጵያ በኮፕ-31 ላይ ለማሳካት ካሰበቻቸው ዋና ዋና ግቦች መካከል፤ የጉባኤውን የድርድር ሂደት ውጤታማ በማድረግ ለኮፕ-32 መሠረት መጣል አንዱ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ-32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በቱርኪዬ አንታሊያ በኮፕ-31 ጉባኤ የምታደርጋቸው ውይይቶች ወደ ተግባራዊ ውጤት እንዲያመሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን በተከፈተበት ወቅት እንዳሉት፤ ከቱርክና ከአውስትራሊያ የጉባኤው ፕሬዚዳንቶች ጋር በቅርበት መሥራት ቀጣይነትና የጋራ ርዕይ እንዲኖር ያግዛል።
ዝግጅቱ ለኮፕ-32 አጋር የሚሆኑ ሀገራትን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትንና የተለያዩ በአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ላይ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማሳተፍ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
በተከፈተው ፓቪሊዮን ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ለኮፕ-32 አዘጋጅነት ብቁ መሆኗ የሚያረጋግጡ 60 ያህል ሁነቶች እንደሚቀርቡ ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የፋይናንስ እድሎችን ለማስፋት አጋርነት የሚፈጠርበት ወሳኝ መድረክ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ዓላማና የምትከተለውን አቅጣጫ በግልጽ ማቅረብ የጋራ መግባባትን ለመፍጠርና የተባባሪዎችን ድጋፍ ለማስፋት ወሳኝ ነው፤ ይህም ጉባኤው የአንድ ሀገር ዝግጅት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ትብብር መድረክ እንዲሆን ያግዛል።
ኮፕ-32 በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተሳትፎን የሚስብ ጉባኤ እንዲሆን ከወዲሁ ግንዛቤ የመፍጠርና የማስተዋወቅ ሥራዎችን ለማከናወን፤ ይህ በቱርክ አንታሊያ የተጀመረው የኮፕ-31 መድረክ መልካም አጋጣሚ ነው።
የተለያዩ ሀገራት፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪል ማኅበራት በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የመድረኩን ተደራሽነትና የሀሳብ ብዝሃነት ያሰፋል።
ከዚህ በተጨማሪ ጉባኤው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ትግል ረገድ እያከናወነች ያለውን ሥራ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
ሀገሪቱ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በደን ልማትና ጥበቃና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ያላትን ተሞክሮ በማቅረብ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያስችላል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ተሞክሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር ለመለዋወጥና አዳዲስ የትብብር እድሎችን ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ ነው፡፡
31ኛው ጉባኤ ለኢትዮጵያ ከምታሰናዳው ቀጣዩ ጉባኤ በፊት የሚኖራትን የዝግጅት አቅም ለማጠናከር፣ የዓለም አቀፍ አጋርነትን ለማስፋትና የጉባኤውን ዓላማ ለማስተዋወቅ ወሳኝ መድረክ ነው።
የኮፕ 32 ስኬት በጉባኤው የሚካሄዱ ውይይቶች ብቻ ሳይሆን፣ ከወዲሁ በሚደረጉ የጋራ ዝግጅቶች፣ በሚገነቡ አጋርነቶችና በሚፈጠር መግባባት ላይም የተመሠረተ ነው።
በመልካም ፈቃዱ

