Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኮፕ32 ሁለገብ የአየር ንብረት ትብብር ዙሪያ እምነትን መልሶ መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው ኮፕ32 ጉባኤ በሁለገብ የአየር ንብረት ትብብር ላይ እምነትን መልሶ መገንባት ቅድሚያ የሚሰጠው ዋነኛ ጉዳይ ነው አሉ የኮፕ32 ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በአንታሊያ፣ ቱርክ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ31) ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም፤ በባለ ብዙ ወገን ማዕቀፍ ውስጥ የምናደርገውን የጋራ ጥረት በሚመለከት፣ እጅግ አስቸጋሪና ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው የተሰባሰብነው ብለዋል፡፡
ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ዓለም አቀፍ ትብብርን እየፈተኑት መሆኑን ገልጸው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በብሔራዊ ደህንነት ዙሪያ እንደገና እየተደራጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በሀገራት መካከል በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ዘርፍ ውድድር በመፈጠሩ ምክንያት የአየር ንብረት ርምጃዎች መሰናክል እየገጠማቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሀገራት የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንን ለመቀነስና የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ከፍ ያለ ራዕይ እንዲኖራቸው እየተጠየቁ ቢሆንም ነባራዊ ሁኔታዎች የዚህ ዓይነቱን ግብ በፋይናንስ መደገፍ ከባድ አድርገውታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የፋይናንስ ክፍተቱ ከተፈታ የአየር ንብረት ለውጥን ጉዳትን መቀነስ ይቻላል፣ የእኛ ተግባር የአየር ንብረት ትብብርን ለታላቅ ዓለም አቀፋዊ አንድነት ምንጭ ማድረግ ነው፡፡
ይህ እምነት፤ ውጤቶችን በማምጣት፣ ሁሉን አቀፍ ሂደትን በመከተል፣ በልዩነቶች ዙሪያ በቁርጠኝነት በመሳተፍ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ራዕይን ከሀገር ውስጥ ትግበራ ጋር በሚያገናኙ ውጤቶች አማካኝነት መገንባት አለበት ነው ያሉት፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
Exit mobile version