አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዳካር የወጣቶች ኦሊምፒክ በፓሪስ ያስከፋነውን ህዝብ የካስንበት ውጤት ነው አሉ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር)።
በ2026ቱ የዳካር ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ አምስት የወርቅ እና ሶስት የብር ሜዳሊያ በማግኘት ከዓለም በቀዳሚነት አጠናቃለች።
ይህንንም ተከትሎ አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፤ በፓሪስ የተመዘገበው ውጤት ደካማ መሆንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ አዝኖብን ነበር ያንን ለመካስ ያደረግነው ዝግጅት ውጤታማ አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል።
በውድድሩ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቶችን ለረጅም ጊዜ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው በዳካር የተመዘገው ውጤት ባለፉት ጊዜያት በሁሉም ውድድሮች እና በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች የተመዘገበ ትልቁ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ የወደፊት ተስፋ ያላቸውን ተተኪ አትሌቶች በማፍራትና በተገቢው ሁኔታ በማዘጋጀት ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ደረጃ የተገኘው ድል በተገቢው ዝግጅትና ስልጠና ዓለም አቀፍ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
በመቀጠልም ለ2028 የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ዝግጅት በመጀመር ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግብ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በእንዳልካቸው ወዳጄ

