Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የካርቦን ልቀት ቅነሳ – የኢትዮጵያ ስኬቶች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ጥረት ትኩረት እየሳበ ይገኛል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ተግባራዊ ምላሽ ለአህጉሪቱ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር አርዓያ የሚሆን ነው።

በፈጣን ኢኮኖሚና በልማት ጎዳና ላይ የምትገኘው ሀገሪቱ፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመከላከል የያዘችው ጽኑ አቋም በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓት ላይ በግልጽ እየተንጸባረቀ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የውሃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይና የጂኦተርማል ኃይል ልማቶችን በስፋት በመተግበር የኃይል አቅርቦት ዘርፏን በጠንካራ መሠረት ላይ እየገነባች ትገኛለች፡፡

ከዚህም ባለፈ የኃይል ዋስትናዋን ይበልጥ ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለመደገፍ የኒውክሌር ኃይልን ለማልማት አቅዳ እየሰራች ነው።

ይህ ርምጃ የሀገሪቱን የኢነርጂ ማዕቀፍ ከማጠናከሩም በላይ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ተግዳሮቶች ለመቋቋም ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ዝግጁነት እንዲያደርግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በተለይም ለአርሶ አደሮች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመስጠትና የአየር ሁኔታ ትንበያን ለማሻሻል የሳተላይት መረጃዎችን እንዲሁም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎችን በስራ ላይ ማዋል ተችሏል።

ይህ ርምጃ በግብርናው ዘርፍ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ከወሰደቻቸው ቁርጠኛ ርምጃዎች መካከል በትራንስፖርት ዘርፉ ሽግግር አንዱ ነው፡፡

የቤንዚንና የናፍጣ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ በማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉን በኤሌክትሪክ ወደሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የማሸጋገር ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ይህ ውሳኔ ለንጹህ ከባቢ አየር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የነዳጅ ጥገኝነትን ለማስቀረትና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ታሪካዊ ርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋቷ እውነተኛ የዜሮ ካርቦን ልቀት ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳያል።

በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትና በዘላቂ የትራንስፖርት ዘርፉ እየወሰደቻቸው ያሉ ርምጃዎች ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላትን ጽኑ አቋም ያሳያሉ።

ሀገሪቱ ከቃላት ባለፈ በተግባር እየፈጸመቻቸው ያሉት እነዚህ ሁለገብ ስራዎች፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም ረገድ ከቀጣናውና ከአህጉሪቱ ባለፈ ለዓለም አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡

#ኢትዮጵያ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation

በእመቤት ሲሳይ

Exit mobile version