አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብን ተሳትፎ በማጠናከር፣ የተሻለ የሥራ አፈፃፀም በማሳየትና በተቀናጀ አሠራር በመንቀሳቀስ በትግራይ ክልል ለውጥና መረጋጋት መጥቷል አሉ የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈፃሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር)።
ባለአደራ አስተዳደሩ በደቡብ ምሥራቅ ዞን እስካሁን ያከናወናቸውን ሥራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች አፈፃፀም ገምግሟል።
ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) የአስተዳደሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትንና የአፈፃፀም ሂደቱን የሚመለከት ሪፖርት ለመድረኩ አቅርበዋል።
የሕዝብ ተሳትፎን ማሳደግና ለሕዝቡ የሚጠቅሙ ሥራዎችን በተሻለ አፈፃፀም ማከናወን ለክልሉ ለውጥና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ የሚታየው ለውጥ የሕዝቡን ተሳትፎ በማጠናከርና በተቀናጀ የሥራ አፈፃፀም በመቀጠል የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተመሳሳይ በግምገማው ላይ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረዳኢ ሃለፎም የአስተዳደሩን የ11 ነጥብ ተልዕኮዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም የባለአደራ አስተዳደሩ በተረከበው ኃላፊነት መሠረት የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የሥራ አቅጣጫዎች አብራርተዋል።
ተልዕኮዎቹ በአስተዳደሩ የሥራ አቅጣጫ ላይ ግልፅነት ከመፍጠር ባለፈ በተለያዩ የአስተዳደር መዋቅሮች መካከል የተቀናጀ አሠራርን ለማጠናከር ያላቸውን ሚና አንስተዋል።
የሁለቱ አመራሮች ሪፖርትና ገለፃ የባለአደራ አስተዳደሩን አጠቃላይ የሥራ አቅጣጫና በደቡብ ምሥራቅ ዞን የተከናወኑ ተግባራትን ለመገምገም መነሻ ሆኗል ነው ያሉት።
በግዛቸው ግርማዬ

