አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ እና የሕዝባችንን የመኖሪያ ቤት ጫና ለማቃለል የሚከናወኑ ስራዎች ተጠነናክረው ይቀጥላሉ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቱሉ ዲምቱ እና በአዲስ ከተማ መርካቶ አካባቢ በተለምዶ ቅጠል ተራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ የተገነቡ ቤቶችን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ ፣ እየተገነባ ያለ ሀገር እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራት እና ቤት የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎች እንዳሉት አንስተዋል፡፡
ከጉባ ብስራቶች አንዱ የዜጎችን የቤት አቅርቦት ችግር በመፍታት የህዝቡን ኑሮ ማሻሻል እንደነበር ጠቁመው፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ይፋ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
እቅዱን ለማሳካትም ዛሬ ጉብኝት የተደረገባቸውን ጨምሮ በአዲስ አበባ ብቻ በተለያዩ ሳይቶች ከ100 ሺህ በላይ ቤቶች እየተገነቡ እንሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ቤቶችን ለመገንባት ሲታቀድ ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የሚጠየቀውን ገንዘብ እንዲሁም እንደ ብረት ሴራሚክ እና መስታዎት የመሳሰሉት ግብዓቶችን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አብሮ ታቅዶ እንደነበር አስታወሰዋል፡፡
በዚህም የግንባታ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን እንዲሁም የፋይናንስ ፈንድ ለማግኘት ከባንኮች በማግኘት በትብብር መስራት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የቤት ግንባታዎችን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ አስችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በዛሬው እለት የተጎበኙት ቤቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የቤት ችግር ለህዝቡ የኑሮ ጫና ምክንያት መሆኑን በመጠቆም፣ ለዚህ ችግር ምላሽ ለመስጠት የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከመንግሥት ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

