አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ እያደገ የመጣውን የነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማመጣጠን መንግሥት፣ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም የግል ባለሀብቶች በተቀናጀ መልኩ የቤት ልማት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች 496 ሺህ 971 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ተላልፈዋል።
ይህ ስኬት በቀጣይ አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት ለተያዘው ሀገራዊ ዕቅድ መሰረት ጥሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ከዚህ ሀገራዊ ፕሮግራም ከፍተኛውን ድርሻ ትወስዳለች።
በመንግሥት ኢኒሼቲቭ እና በከተማ አስተዳደሩ በጀት የሚከናወኑ ግንባታዎች የመኖሪያ ቤት አቅርቦቱን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በጋራ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራም ተመዝግበው ሲጠብቁ ለነበሩ ነዋሪዎች 139 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአራብሳ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ገላን ጉራ፣ ቃሊቲ ወርቁ ሰፈር እና ቱሉ ኤጀርሳን ጨምሮ በ18 አዳዲስ ሳይቶች የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን በመንግሥት ኢኒሼቲቭ እና በበጎ ፈቃደኛ ባለሀብቶች ትብብር በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች እንደ ቅጠል ተራ እና ካዛንቺስ ባሉ አካባቢዎች ለሚገኙ የልማት ተነሺዎች ዘመናዊ መንደሮች ተገንብተው እየተላለፉ ይገኛሉ።
የመንግሥትና የግል አጋርነት እንዲሁም ባለሀብቶች ተሳትፎ የቤት ልማት ሥራውን እያጠናከረ ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩ መሬት አቅራቢነት እና በባለሀብቶች ፋይናንስ 120 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ስምምነት ተፈርሞ የ55 ሺህ ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል።
የግል ሪል ስቴት አልሚዎችም ዝቅተኛ የትርፍ ህዳግ ይዘው ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ቤቶችን እንዲያቀርቡ እየተበረታታ ይገኛል።
ሌላው ደግሞ ነዋሪዎችና የመንግሥት ሠራተኞች በመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚደረገው ድጋፍም ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ለተደራጁ ማህበራት መሬት እና መሰረተ ልማት በነጻ በማቅረብ ግንባታ እንዲያካሂዱ እያደረገ ሲሆን፤ ለዚህም 6 ሺህ 194 መምህራን በ57 ማህበራት ተደራጅተው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የቤት ግንባታ እንዲጀምሩ መደረጉ በአብነት ይጠቀሳል።
በተመሳሳይ መልኩ 119 የተደራጁ የቤት ሥራ ማህበራት መሬት ተረክበው ከ13 ሺህ 600 በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ጀምረዋል።
ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ባሻገር የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ እና የፋይናንስ አቅምን ለመገንባት የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።
እነዚህ ሥራዎች መዲናዋን ለኑሮ ምቹ የሚያደርጉ እና ተመራጭነቷን የሚጨምሩ ናቸው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በእመቤት ሲሳይ

