አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያ የንግድ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ከብሔራዊ ጥቅም፣ ከሉዓላዊነትና ከትውልድ ተሻጋሪ ብልፅግና ጋር የተያያዘ ስትራቴጂያዊ ጉዳይ ነው።
በአፍሪካ ከሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፣ የባሕር በር አልባ መሆኗ በውጭ ንግድ፣ በሎጂስቲክስ፣ በትራንስፖርትና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስሯ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ የግድ ብሏታል።
የባሕር በር ማጣት በሀገሪቱ የንግድ አቅምና በውጭ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ የተለያዩ ገደቦችን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህንኑ ሁኔታ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለመቀየር የሚደረገው ጥረት የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ጥቅም አካል ነው።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷና በልማት አቅሟ ላይ ተመሥርታ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ማሳካት መቻሏን እያሳየች ትገኛለች። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚህ ጉልህ ማሳያ ነው።
ለዘመናት ለልማት ሳይውል የቆየውን የዓባይ ወንዝን በማልማት፣ የኃይል ምርትን ለማሳደግና የኢኮኖሚ አቅምን ለማጠናከር የተከናወነው ይህ ታላቅ ሥራ በሀገራዊ አንድነትና ቁርጠኝነት የሚገኝን ውጤት ያሳያል።
የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውም ጥረት በተመሳሳይ መልኩ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ነው። ይህም ከአጭር ጊዜ ፍላጎት ባለፈ፣ ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድል፣ የንግድ አማራጭና የልማት መሠረት ለመፍጠር ያለመ ነው።
በኢኮኖሚ የበለፀገች፣ በዓለም አቀፍ መድረክ የተከበረችና ተወዳዳሪ የሆነች ሀገር መገንባት የሚያስችሉ መሠረቶችን መጣል የባሕር በር ጥያቄዋ ዋነኛ ዓላማ ነው።
የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ማልማት፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ፣ የንግድ ትስስርን ማስፋፋትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የዚህ ስትራቴጂ አቅጣጫዎች ናቸው።
የባሕር በር ተጠቃሚነት መረጋገጥ በተለይም ለውጭ ንግድ ዕድገት ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ፣ የወደብ አገልግሎትን በተሻለ ሁኔታ ማግኘት የገቢና የወጪ ምርቶችን የማጓጓዣ ወጪና ጊዜ ለመቀነስ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በተሻለ ዋጋ ለማቅረብ ይረዳል።
የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከርና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም ከአህጉራዊ እና ከዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ጋር ያለውን ትስስር በማሳደግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ያሰፋል።
የኃይል ልማትን፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያን፣ የቱሪዝም ዘርፍንና የክልላዊ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከርም አዳዲስ ዕድሎችን ይፈጥራል። ይህም የሥራ ዕድል እንዲስፋፋ፣ የዜጎች ገቢ እንዲያድግና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም እንዲጠናከር የሚያግዝ ነው።
ኢትዮጵያ በግፍ እና በሴራ ከተገለለችበት የባሕር በር ለመመለስ እያደረገች የምትገኘው እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ መርህን የተከተለ፣ የሀገራትን ሉዓላዊነትና የጋራ ጥቅም ባከበረ መልኩ የሚተገበር ነው።
ለዚህም ጠንካራ ዲፕሎማሲ፣ የዓለም አቀፍ ሕግን ያከበረ አካሄድ፣ የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም ውይይትና ትብብር ወሳኝ ናቸው። ጉዳዩ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው የጋራ ዕድገትና መረጋጋትም ጠቀሜታ አለው።
የሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ነፃነት፣ የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነትና የወደፊት የልማት አቅም ከሚወስኑ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ሀገራዊ ጥቅምን በጋራ አጀንዳነት በመያዝ፣ በአንድነትና በቁርጠኝነት መሥራት ትልቅ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ እንደመሆኑ፣ የባሕር በር የማግኘት የዛሬው ጥረትም ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለ የልማት፣ የንግድና የብልፅግና ዕድል የሚያመቻች ነው።
በምሕረት ደምሴ

