አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ2027 የሚካሄደውን የአፍሪካ ንግድ ትስስር ጉባኤ (ACCS) እንድታስተናግድ የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የጉባኤው መሥራች ናይጄል ኮሊን ታተርሳል፣ የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ፋና አባይ እና የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማኅበር ፕሬዚዳንት ይልቃል አባተ ተፈራርመዋል።
ከ1 ሺህ በላይ የንግድ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና ፈጣሪዎችን በአዲስ አበባ የሚያሰባስበው ጉባኤው፣ በአፍሪካ የማርኬቲንግ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአቅርቦት ሰንሰለትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም የፈጠራ ኢኮኖሚ ዘርፎችን በማስተሳሰር አዳዲስ የንግድ ዕድሎችን ለመፍጠርና አህጉራዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ፋና አባይ በዚህ ወቅት፤ ጉባኤውን ማስተናገድ ለኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎችና ኩባንያዎች የአፍሪካ ገበያዎችን በስፋት ለመድረስ፣ አዳዲስ የንግድ አጋርነቶችን ለመፍጠርና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የጉባኤው መሥራች ናይጄል ኮሊን ታተርሳል በበኩላቸው፤ በዛምቢያ የተጀመረውን የጉባኤውን ስኬት ኢትዮጵያ በማስቀጠል አህጉራዊ ተሳትፎውን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምታሳድገው ጠቁመዋል።
የጉባኤውን ዝግጅት የኢትዮጵያ ማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማኅበርና የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማኅበር ከኢትዮጵያ ሎጂስቲክስና አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ባለሙያዎች ማኅበርና ከተለያዩ አህጉራዊ ተቋማት ጋር በመተባበር በጋራ እንደሚመሩት ተመላክቷል።
በዘመን በየነ

