አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ድል ከውጭ የምግብ ጥገኝነት በማላቀቅ ራስን የመቻል ማሳያ እያደረጋት ይገኛል።
በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተከናወኑት ሰፊ ስራዎችና የተገኙት አስደናቂ ውጤቶች የሀገሪቱን ከፍታ የሚያሳዩ፣ በታሪክ የሚዘከሩ ትላልቅ ምዕራፎች ናቸው።
ይህ ታላቅ ስኬት በሙከራ ደረጃ በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ የተጀመረ ሲሆን፤ ጅምሩን በማስፋት በ2018 ዓ.ም ብቻ ወደ 3 ነጥብ 78 ሚሊየን ሄክታር ከፍ ማለት ችሏል።
ይህ የመሬት ሽፋን እድገት አስደናቂ የምርት መጠን እንዲመዘገብ በር ከፍቷል።
ለአብነት ያህል በ2017 ዓ.ም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ 140 ሚሊየን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን፤ በ2018 ዓ.ም ደግሞ ይህ አሃዝ አድጎ 149 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት በበጋ መስኖ ልማት መሰብሰብ ተችሏል።
ይህን የልማት አብዮት በማስቀጠል በዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 189 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው፡፡
ይህም ሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ስትቸገርበት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ቀውስ በማቃለል ረገድ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስንዴ ከውጭ ለማስገባት በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ታወጣ የነበረ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ ምርት ፍላጎቱን በመሸፈን ወጪውን ማስቀረት ተችሏል፡፡
ከዚህም በላይ ልማቱ ድርቅ በሚያጠቃቸው ቆላማ አካባቢዎች ጭምር የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም ሰፋፊ የስንዴ ማሳዎችን ማልማት ተችሏል፡፡
ይህ ውጤታማ ትግበራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት መሳብ የቻለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዚህ የልማት ስኬት ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የአግሪኮላ ሜዳሊያ የክብር ሽልማት ተበርክቶላታል።
የዚህ ታላቅ ለውጥ ስኬት በዕድል የተገኘ ሳይሆን በዘመናዊ የቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦትና የአሰራር ማሻሻያዎች የታገዘ ነው።
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በኩታ ገጠም እንዲያለሙ በማድረግ በትራክተር ማረስና በኮምባይነር መሰብሰብን የመሳሰሉ የመካናይዜሽን አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ተደርጓል።
ለቆላማና ለደጋማ አካባቢዎች ፍጹም ተስማሚ የሆኑ፣ በሽታን የሚቋቋሙ የስንዴ ዝርያዎች ተዘጋጅተው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የቻለችና የምግብ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

