አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ መነሻ፣ የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት እንዲሁም በአስደናቂ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር የታደለች ሀገር ናት።
የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በመውሰድ፤ ነባር ቅርሶችን ከማደስ ባለፈ አዳዲስና ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባት ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ እያሳደገ ይገኛል።
የቱሪዝም ዘርፉ ከግብርና፣ ከኮንስትራክሽን፣ ከትራንስፖርትና ከንግድ ዘርፎች ጋር ባለው ጥብቅ ትስስር ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ወሳኝ አቅም ሆኗል።
ዘርፉ ለሀገሪቱ ፈጣን የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዋነኛ ምንጭ ከመሆኑም በላይ በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፈጥሯል።
በተለይም በሆቴል፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በትራንስፖርት፣ በዕደ-ጥበብና በግብርና ምርቶች አቅርቦት ለዜጎች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
በተጨማሪም ዜጎች የሀገራቸውን ታሪክና ተፈጥሮ የመጎብኘት ባህላቸው እያደገ በመምጣቱ በሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ እንዲንቀሳቀስና የአካባቢው ማህበረሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል።
በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የአዳዲስ መዳረሻዎች መስፋፋትና የአየር ትራንስፖርት ትስስር መጠናከር የጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አሳድገውታል።
በሌላ በኩል መዲናዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ፤ በከተማዋ በተከናወኑ የኮሪደር ልማትና ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ግንባታ የኮንፈረንስ ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
በዚህም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን በማስተናገድ የአፍሪካ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ይበልጥ አጠናክራለች።
የዘርፉን ዕድገት ዘላቂና ተወዳዳሪ ለማድረግ መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል የግል ባለሀብቶች በሆቴል፣ በሪዞርትና በመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ የሚያበረታቱ የቀረጥ እፎይታዎች፣ የመሬት አቅርቦት ማበረታቻዎችና የመንግሥትና የግል አጋርነት አሠራሮች ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም የውጭ ጎብኚዎችን ጉዞ ለማቀላጠፍ የተጀመሩ ዲጂታል አሠራሮች ለጎብኚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል።
በዚህ ረገድ የኦንላይን ቪዛ (e-Visa) እና በአውሮፕላን ማረፊያ ቪዛ አገልግሎት (Visa on Arrival) እንዲሁም በዲጂታል አማራጮች የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ሥራዎች ይጠቀሳሉ።
ተፈጥሮን ሳይጎዱ የሚለሙ የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፍ ፖሊሲው ዋነኛ ትኩረቶች ሆነዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ማሻሻያዎችና የመዳረሻ ልማቶች የጎብኚዎች ቁጥርና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር በማድረግ ዘርፉ ለሀገራዊ ብልጽግና ያለውን ሚና አሳድገዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በትዕግስት ግዛቸው

