Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራትን እየከናወነች ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተላላፊ በሽታዎችን ሥርጭት አስቀድሞ በመግታትና የላቀ የመከላከል አቅም በመገንባት የጤና ሉዓላዊነቷን እያጎለበተች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
በጤና ሚኒስቴር፣ በአርማወር ሃንሰን ምርምር ኢንስቲትዩትና በአንትወርፕ ትሮፒካል ሜዲሲን ኢንስቲትዩት ትብብር የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የተላላፊ በሽታዎች መከላከል ሳይንሳዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው ለተላላፊ በሽታዎች መጨመር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመዳሰስ ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱ ምክረ ሐሳቦች የሚፈልቁበት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ውጤታማነት የሚያሳድጉ ዘመናዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ነው።
የወረርሽኞችን ሥርጭት በመግታት ለዓለም የጤና ሥርዓት ውጤታማነት ተምሳሌት የሆነ ትልቅ ስኬት ማምጣቷን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሏም ለተላላፊ በሽታዎች ሥርጭት መከላከል አቅም መገንባቷን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በርካታ የጤና ኬላዎችን በማቋቋም የጤና ክብካቤን ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የክትባት ተደራሽነትን ለማስፋት ክትባትን በምርምር የማውጣት ሥራም በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለመድኃኒት አምራቾች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች ነው ያሉት፡፡
በጉባኤው ላይ ተመራማሪዎች፣ የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
Exit mobile version