አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሊወያዩ ነው፡፡
የሦስቱ ሀገራት መሪዎች በመጪው ሀሙስ ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደርጉት የሦስትዮሽ ስብሰባ ላይ ስለ ዓለም ሰላም እንደሚነጋገሩ ተገልጿል፡፡
የመሪዎቹ ስብሰባ በቻይናዋ ሼንዠን ከተማ ከሚካሄደው የእስያና ፓስፊክ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ ጎን ለጎን እንደሚካሄድ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባይዋ በሰጡት መግለጫ፤ የሦስቱ ሀገራት ፕሬዚዳንቶች ውይይት ታሪካዊና ለዓለም ሰላም መሠረታዊ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል፡፡
መሪዎቹ የዓለምን ሰላም በማስጠበቅና በሀያላን ሀገራት ግንኙነት ውስጥ ስትራቴጂያዊ መረጋጋትን በማስፈን ዙሪያ በጥልቀት እንደሚመክሩ አመልክተዋል፡፡
ቻይና፣ ሩሲያ እና አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሀገራቱ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን በመፍታት የዓለምን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር የጋራ ጥቅም መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ፍላጎት ነው ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በእመቤት ሲሳይ

