አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በኮሪደር ልማትና በወንዞች ዳርቻ የልማት ሥራዎች ያሳየችው ተሞክሮ በትብብር ለመሥራት የሚያግዝ ነው አሉ የጀርመኗ ላይፕዚሽ ከተማ የአካቶ ባህልና ትምህርት ዳይሬክተር ጃና ዘህለ።
አዲስ አበባ በአካታች የከተማ ልማት ዘርፍ ያካበተችውን ተሞክሮ ለጀርመኗ እህት ከተማ ላይፕዚሽ እያጋራች ሲሆን፣ በዚሁ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ባለፉት 5 ዓመታት መዲናዋ ስማርት ከተማ ለመገንባት ባደረገችው ጥረት የተከናወኑ አካታች የልማት ሥራዎች ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
ሥራዎቹ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም ክፍል ያሳተፈ የከተማ ልማት እውን ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ከላይፕዚሽ ከተማ የመጡት የልዑካን ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 5 ዓመታት የተመለከቱት ለውጥና የተከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዳስደነቋቸው ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው የሚቀስሟቸው ተሞክሮዎች በራሳቸው ከተማ ለሚያከናውኗቸው የተለያዩ ሥራዎች ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆኑም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
የላይፕዚሽ ከተማ የአካቶ ባህልና ትምህርት ዳይሬክተር ጃና ዘህለ በዚህ ወቅት፤ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ በኮሪደር ልማትና በወንዞች ዳርቻ ያከናወነቻቸው አካታች የልማት ሥራዎች አብሮ ለመሥራት የሚያግዝ ነው ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

