አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕገወጡ ህወሓት የጦርነት ዝግጅት፣ የግዳጅ ምልመላና ለጦርነት ዓላማ የተደረገው ኢኮኖሚያዊ ጫና የትግራይን ሕዝብ ለከፍተኛ ድህነት ዳርጎታል አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የአስተዳደርና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈፃሚ አቶ አሰፋ አብረሃ።
አቶ አሰፋ አብረሃ ይህን ያሉት በመቐለ ከተማ ከተባበሩት መንግሥታት ልዑካን፣ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በሚካሄደው ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
አቶ አሰፋ በዚህ ወቅት፤ የችግሩ ተጎጂዎች ተፈናቃዮች ብቻ ሳይሆኑ፣ በትግራይ የሚኖሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ብለዋል።
በዚህም የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም የክልሉ ዋና ከተማ መቐለ ነዋሪዎች ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሕገወጡ ህወሓት የትግራይ ክልልን ለቆ ሲወጣ በክልሉ የመንግሥት ተቋማትና የአስተዳደር መዋቅሮች ላይ የፈጸመውን ውድመትና ዝርፊያም አውግዘዋል።
የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልሉ ፓርላማና ሌሎች የመንግሥት ቢሮዎች በእሳት መውደማቸውን፣ የቢሮ ዕቃዎችና ሰነዶች መዘረፋቸውን፣ የመረጃ መረቦችና ኮምፒውተሮች መውድርማቸውን አስረድተዋል።
በዚህም ምክኒያት የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዳያከናውኑ እንቅፋት መሆኑን አብራርተዋል።
የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሰላምና ፀጥታን ማስፈን፣ የመንግሥት አስተዳደርና መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ፣ ኢኮኖሚያዊ ማገገምን ማፋጠን፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ ብሎም ለምርጫ የሚያስፈልጉ ተቋማዊ ዝግጅቶችን ማጠናቀቅ ዋነኛ ተልዕኮዎቹ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በግዛቸው ግርማዬ

