አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ልማት በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባን ሀገር በማነጽ አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እያበሰረ ነው አሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሰው ልጆች የዘር ሀረግ የሚመዘዝባት ምድረ ቀደምትና በመንግሥት አስተዳደር ቀዳሚ የሥልጣኔ ባለቤት ናት።
የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ገናና ሥልጣኔም በዓባይ ወንዝ ባለቤትነት፣ የሰው ዘርና የቡና መገኛነት፣ በዓድዋ ከተጎናጸፈችው ነጻነትና የብርቅዬ ሀብቶች መገኛነት የሚመነጭ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ለዓለም ያበረከተቻቸው ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶችና እሴቶች የምትታወቅባቸው ልዩ መገለጫዎቿ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የመደመር መንግሥት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ብዝኃ የኢኮኖሚ ልማት የሰጠው ትኩረትም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን ያሰናሰለ አዲስ የሥልጣኔ ብርሃን መፈንጠቁን ተናግረዋል።
ይህም የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ ማንነትና ሀገራዊ አንድነት ሚዛን የሚያስጠብቅ ፍትሐዊና አካታች ምኅዳር በመገንባት ወንድምና እህትማማችነትን በእጅጉ እያጎለበተ መሆኑን አንስተዋል።
የዜጎች የአብሮነት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላትም ሉዓላዊ አንድነቷ የተጠበቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰረት እየጣሉ መሆኑን አብራርተዋል።
የመደመር መንግሥት የብዝኃ ኢኮኖሚ ልማት ለቱሪዝም ዘርፍ የፈጠረው ዕድልም ታሪካዊ ሀብቶችን በመጠበቅ የሀገርን ውድ የቅርስ ሀብቶች መጠበቅ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በተለይም የመደመር መንግሥት ለመንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርስ ልማትና ጥበቃ የሰጠው ልዩ ትኩረት ክብርን የሚያጎናጽፍ የትውልድ ግንባታ ትርክትን በማስረጽ የሀገርን ማንነትና መመኪያነት እንዲያገለግል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችና የሕዝብ እሴቶችም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በአዲስ አበባ ጨምሮ የአጼ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፣ የጅማ አባጅፋር፣ የሀረር ጀጎል ግንብና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች ዕድሳት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ አስቻይ የቱሪዝም ምኅዳር እንዲላበሱ አድርጓል ነው ያሉት።
የመደመር መንግሥት የባህልና ቱሪዝም ልማት በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባን ሀገር በማነጽ አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እያበሰረ መሆኑን ገልጸው ይህም አሰባሳቢና የወል ትርክትን የሚያንጽ ዐሻራን በማንበር በትውልድ ቅብብሎሽ የምትገነባ ኢትዮጵያን ታላቅነት እያበሰረ ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

