Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኮፕ 32 – ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ)  ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) ታስተናግዳለች፡፡ በጉባኤው ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረክነት ባለፈ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ  ዕድልን ይዞ ይመጣል።

ኢትዮጵያ ጉባኤውን በጥራት ከማስተናገድ ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ወደ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) እና ወደ ዘላቂ ልማት ለመቀየር አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራዎች ማጠናቀቅ ይጠበቅባታል።

ከዚህ በፊት ጉባኤውን ያስተናገዱ ሀገራት ሁነቱን ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ገጽታቸውን ለማሳደግ፣ ጎብኝዎችን ለመሳብ፣ ለመሰረተ ልማት ማሻሻያ እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቅመውበታል፡፡

ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ (ኮፕ 32) ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራዎች እያካሄደ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ከኮሚቴው ጋር አጠቃላይ የዝግጅት ሥራ ሂደቱን በገመገሙበት ወቅት እንዳሉት ኮፕ 32 ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመሆኑ ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት እና የአካባቢ ጥበቃ አጀንዳን ለማራመድ፣ አጋርነትን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም ብሔራዊ ጥረቶቻችንን ወደ ዘላቂ ውጤት ለመለወጥ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችንና የአየር ንብረት ፋይናንስ ተቋማትን ለመሳብ ሰፊ አቅም አላት። ሰፊ አቅም ብቻ ሳይሆን በፖሊሲ የተደገፈ የመንግሥት-የግል አጋርነትን የሚያበረታታ አሰራርን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

በውኃ፣ በፀሐይ፣ በነፋስና በእንፋሎት ኃይል ልማት፣ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሠረተ ልማት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና፣ በደን ልማትና በካርበን ገበያ ዘርፎች ያሏት ዕድሎች ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች፡፡

ይህንን ዓለም አቀፍ የትኩረት ማዕከል የሆነ ጉባኤ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለመለወጥ፣ ኢትዮጵያ ለባለሀብቶች የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችን አስቀድማ አዘጋጅታ እየሰራችበት ነው።

ለዚህም በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይል፣ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢንቨስትመንት አቅሟን፣ የአሰራር ማሻሻያዎችንና ማበረታቻዎችን እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡

አሁንም ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም አሟጥጦ ለመጠቀም ጉባኤው የሚፈጥረውን አጋጣሚ በሚገባ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሀብት መለወጥ ይገባል፡፡

ከአምስት ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ነው፡፡ በጉባኤው ወቅት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ከ80 ሺህ በላይ የሀገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የንግድ ሰዎች የሆቴል፣ የአቪዬሽን እና ቱሪዝምን በማነቃቃት፣ በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ዘላቂ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

የኮሪደር ልማቶች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አጠቃቀም፣ ሌሎች የመሰረተ ልማቶች እና የከተሞች የአገልግሎት መስጫ ሥርዓቶችን የበለጠ በማዘመን የሀገሪቱን ገፅታ ከመገንባት ባሻገር የኮንፈረንስ ቱሪዝም አቅሟን ለማጉላት ያስችላል፡፡

በአጠቃላይ፤ ኮፕ 32 ለኢትዮጵያ ዘላቂ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የአፍሪካን የአየር ንብረት አጀንዳ በመምራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምትገነባበት ታሪካዊ ምዕራፍ ሊሆን ይገባል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ #ኮፕ_32_ኢትዮጵያ #COP31 #COP32 #COP32ETHIOPIA #fanamediacorporation

በቴዎድሮስ ሳህለ

Exit mobile version