አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል መንግሥት የህግ ማስከበር ርምጃ ሕገወጡን የህወሓት ቡድን ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ በማውረድ ሕዝቡ የሰላም አየር እንዲተነፍስ አስችሏል፡፡
በክልሉ የተቋቋመው የባለአደራ አስተዳደርም በህግ ማስከበር ተግባራት የተገኘውን ሰላምና ጸጥታን የማፅናት፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን መልሶ የማስጀመር፣ የመልሶ ግንባታና አዳዲስ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ በክልሉ የሰላም አየር መንፈስ ከጀመረ ሰነባብቷል፤ ሕዝቡም ሙሉ በሙሉ ወደ ዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው እየተመለሰ ነው፡፡
በውሸት ፕሮፓጋንዳ ተታልለውና በግዳጅ ከህገወጡ ቡድን ጋር ተሰልፈው የነበሩ ታጣቂዎችም በሰላም እጃቸውን በመስጠትና ትጥቅ በመፍታት፣ በተሃድሶ ስልጠናና በመልሶ ማቋቋም ሂደት አልፈው ማህበረሰቡን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ልኡካን ቡድን፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ወደ መቐለ በማቅናት በክልሉ ያለውን አሁናዊ እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ይገኛሉ፡፡
ልዑካኑ ከክልሉ ባለአደራ አስተዳደር እንዲሁም ከሀይማኖት አባቶች ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት መቐለ ከተማ የሚገኘውን የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ማዕከል ጎብኝተዋል።
የልዑካኑ ውይይትና ጉብኝቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ፣ በተፈናቃዮች አያያዝ ሁኔታ፣ የትጥቅ መፍታትና መልሶ ማቋቋም ሂደት ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የዓለም አቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ወደ ትግራይ ክልል መጓዝ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማረጋገጥ ተግባራት በአስተማማኝ ሂደት ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ቡድኑ በትግራይ ክልል ጉብኝት ማድረጉ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጠሩ አንዳንድ አሉታዊ አመለካከቶችን ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በተለያዩ የድጋፍና መልሶ ግንባታ ተግባራት ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን ለማስገንዘብ ይረዳል።
የትግራይ ሕዝብ አሁን ያገኘውን ሰላምና ጸጥታ በማፅናት፣ የተጀመሩ አገልግሎቶች የበለጠ እንዲሟሉና በክልሉ ዘርፈ ብዙ ልማት እንዲመጣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

