አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ32) ለማስተናገድ መመረጧ ከፍተኛ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም ለማስተዋወቅና ገጽታዋን ለመገንባት ወርቃማ ዕድል ይፈጥርላታል።
የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ80 ሺህ በላይ የጉባኤው ተሳታፊዎችና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሲሆን፤ ሁነቱ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም በማሳየት ጎብኚዎችንና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ጥንታዊ ታሪክና ብዝሃ ባህል ባለቤት፤ የሰው ዘር መገኛ፣ የቡና መገኛ፣ የታላላቅ አትሌቶች መፍለቂያና ማራኪ የተፈጥሮ መልክዓ ምድር የታደለች ድንቅ ሀገር ናት።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመደመር መንግሥት የቱሪዝም ልማት በመዲናዋና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡ አዳዲስ መዳረሻዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም አማራጮች ለማብዛት ያስቻሉ ናቸው።
እነዚህን ሀብቶች ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጋር በማስተሳሰር ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆነ ኢኮ-ቱሪዝምንና የማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝምን ማስፋፋት የየአካባቢዎቹን ማህበረሰብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ይህንን ዓለም አቀፍ ጉባኤውን በስኬት ከማስተናገድ ባለፈ፤ የቱሪዝም ዘርፉን በዘላቂነት ለማሳደግ የሚያስችል ምቹ መደላድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት ይገባል፡፡
ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤን ያስተናገዱ ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው፤ ሀገራቱ ጊዜያዊ የጉባኤ ዝግጅቶችን ወደ ዘላቂ የመሰረተ ልማትና የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ እድገት በመቀየር የሁነቱን ትሩፋት በሚገባ መጠቀም ችለዋል።
ለኮፕ32 የሚገነቡ ዘመናዊ የስብሰባ ማዕከላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርትና የዲጂታል አገልግሎቶች የኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት የበለጠ ለማጉላት ያስችላሉ።
ይህንን ዕድል ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር በመንግሥት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ዘንድ የተቀናጀ ሥራ ይጠይቃል።
ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅትና በኋላ ለልዑካን የሚሆኑ ልዩ የጉብኝት ጥቅሎችን ማዘጋጀት፣ የመስተንግዶ ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታትና ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማስተዋወቂያ ዘመቻዎችን በስፋት መጠቀም አስፈላጊ ነው።
ኮፕ32 ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ተግባራዊ ርምጃዎች ባሻገር፤ የተፈጥሮና የባህል ሀብቷን በመጠበቅ፣ የአገልግሎት ዘርፏን በማዘመንና ለዜጎቿ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘላቂ የቱሪዝም ኢኮኖሚ የምትገነባበት የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው።
ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ከጉባኤው በኋላ የኢትዮጵያ ቱሪዝም፣ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ አቅምና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የሚኖራት ገፅታ ወደ አዲስ ምዕራፍ ከፍ ማለቱ አያጠያይቅም፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

