አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ለቡና ልማት በሰጠው ትኩረትና ባመቻቸው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ጥራት ያለው ቡና በማምረት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ውጤታማ ሆነናል አሉ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን የቡና አልሚ ባለሀብቶች።
በዞኑ በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ፈይሰል አባመጫ፤ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትና ባመቻቸው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ በ16 ሳይቶች ላይ የቡና ልማት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በባለፈው የምርት ዘመን 9 ቶን ቡና መሰብሰባቸውን አስታውሰው ከዚህም 25 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ማስገኘት መቻላቸውን ጠቁመዋል።
በዞኑ ጎማ ወረዳ፤ በቆታ ጮሃ ቀበሌ በቡና ልማት የተሰማሩት ሌላኛው ባለሀብት አቶ መንሱር አባሂከም በበኩላቸው፤ በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለ20 ዓመታት በቡና ልማት ሥራ መሰማራታቸውን ጠቁመው የቡና ተክሎችን በአግባቡ በመንከባከብና የምርት ጥራትን በማሻሻል ስፔሻሊቲ ቡና ማምረት እንደቻሉ ተናግረዋል።
በመንግሥት በተመቻቸው ዕድል ተጠቅመው በ50 ኩንታል ቡና የጀመሩት ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ 6 ኮንቴይነር ቡና በማምረትና ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ደረጃ መድረሱን ንውነ የገለጹት።
ባለሀብቶቹ የቡናን ጥራት በመጠበቅና በልማቱ ላይ በመሳተፍ ገቢያቸውን ማሳደግና የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል መቻላቸውንም አስረድተዋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ለሚከበረው 21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበር አካል በዞኑ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ የሚገኙ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮችም፣ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን እየተከናወነ ያለው የቡና ልማት ሥራ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በወርቅአፈራው ያለው

