አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ፅምብላ ወረዳ ከሕገወጡ የህወሓት ቡድን ጋር ሸፍተው የነበሩ ከ200 በላይ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል እጃቸውን ሰጡ።
ታጣቂዎቹ በወረዳው በረሃማ አካባቢዎች ተሰማርተው የቆዩ ሲሆን፤ የተፈጠረላቸውን የሰላም አጋጣሚ በመጠቀም፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን ሰጥተዋል።
ወደ መደበኛ ሰላማዊ ሕይወታቸው ለመመለስ መወሰናቸውን ተከትሎ፤ በዞኑ አመራሮችና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች አቀባበል ተደርጎላቸወዋል፡፡
በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ ኤፍሬም በዚሁ ወቅት፤ ታጣቂዎቹ የጥፋት መንገድን ትተው ሰላምን በመምረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
ሠራዊቱ ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥና አሁንም በተሳሳተ መንገድ በረሃ የቀሩ ታጣቂዎች የእነዚህን ወገኖች አርአያ በመከተል የሰላም አማራጩን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዞን አመራሮች በበኩላቸው፤ የክልሉ ሕዝብ ከጦርነትና ከመፈናቀል ወጥቶ ወደ ልማትና ዳግመ ግንባታ መሸጋገር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ወደ ሰላም የተመለሱት ወገኖች አስፈላጊው የተሃድሶ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉና በልማት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እጃቸውን የሰጡት ታጣቂዎች ስህተታቸውን አምነው ለአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጥና ለልማት ሥራዎች መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ

