Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት የትብብር መድረክ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ጤና የሀገራት የግል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻግሮ የጋራ ትብብርን፣ የሳይንስ እውቀትንና የተቀናጀ ርምጃን የሚጠይቅ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ወረርሽኞችን መከላከል፣ የጤና አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የመድኃኒትና የክትባት አቅርቦትን ማረጋገጥ እንዲሁም የጤና ሥርዓትን የመቋቋም አቅም ማጠናከር የሀገራት የጋራ ትኩረቶች ናቸው፡፡
ይህንን የጋራ ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያግዘው አህጉራዊ የልምድ፣ የእውቀትና የመፍትሔ ልውውጥ መድረክ የሆነው አምስተኛው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ከሕዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው በኢትዮጵያ መንግሥትና በአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) በጋራ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የዘንድሮው ጉባኤም አፍሪካ በጤና ዘርፍ በውጭ ድጋፍና አቅርቦት ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ፣ በራሷ ሀብት፣ እውቀት፣ ቴክኖሎጂና የምርት አቅም የሕዝቦቿን ጤና የምትጠብቅበትን ሥርዓት እንድትገነባ ያበረታታል።
የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲመረምሩ፣ የተሳኩ ልምዶችን እንዲለዋወጡና ተግባራዊ መፍትሔዎችን እንዲያዘጋጁ ዕድል መፍጠር ሲሆን በጉባኤው የፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የጤና እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በአንድ መድረክ በመገናኘት በአህጉሪቱ የጤና ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ይወያያሉ።
አዳዲስና ተደጋጋሚ የበሽታ ወረርሽኞችን ቀድሞ የመለየት፣ የመከላከልና በተቀናጀ መንገድ ምላሽ የመስጠት አቅምን ማጠናከር፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የዲጂታል ጤና መረጃና ዘመናዊ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጤና አገልግሎትን ማሻሻል፤ በአህጉሩ የመድኃኒት፣ የክትባትና የሕክምና መሣሪያዎች ምርትን በማሳደግ የውጭ ጥገኝነትን መቀነስ የጉባዔው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
የጤና ዘርፍ የሀገር ውስጥ ፋይናንስን ማጠናከርና ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ የሆነ ፍትሐዊ አገልግሎትን ማረጋገጥ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በሕዝብ ጤና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመቀነስ የጤና ሥርዓቶችን የመቋቋም አቅም ማሳደግ የሚደረጉት ውይይቶች በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፉ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት፣ የአፍሪካን የጋራ የጤና ስትራቴጂ ለማጠናከርና የሕዝቦችን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል ወሳኝ ናቸው።
ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ማስተናገዷዓለም አቀፍ ሚናዋን የበለጠ ከማጠናከሩም በላይ የአፍሪካን የጤና ዘርፍ ማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ የሚያስችላት ሲሆን፤ በርካታ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የእውቀትና የትብብር ዕድሎችን ይፈጥራል።
ከተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ክፍሎች የሚመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች በሀገሪቱ መገኘታቸው ለሆቴልና ቱሪዝም፣ ለትራንስፖርት፣ ለንግድና ለተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ተጨማሪ የስራ ዕድል ይፈጥራል። ይህም የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴን በማበረታታት የገቢ ምንጮችን ለማስፋፋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ጉባኤው የኢትዮጵያን ቅርሶች፣ ባህላዊ እሴቶች፣ የተፈጥሮ መስህቦችና የከተማ ልማት ሥራዎች ለዓለም ማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ ነው። የጉባኤው ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ቆይታ ሀገሪቱን እንደ ቱሪዝምና የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች መዳረሻ ለማስተዋወቅ ያግዛል።
ጉባዔው የጤና ዘርፍ ባለሀብቶችን፣ የመድኃኒት አምራቾችን፣ የቴክኖሎጂ ተቋማትንና የምርምር ማዕከላትን በአንድ መድረክ ማገናኘቱ በኢትዮጵያ የጤና ኢንዱስትሪ ልማት፣ በመድኃኒት ምርት፣ በሕክምና ቴክኖሎጂና በምርምር ዘርፎች አዳዲስ የትብብርና የኢንቨስትመንት እድሎችን ይከፍታል፡፡
አዲስ አበባ ጉባኤውን ማስተናገዷ አፍሪካ የጤና ዕጣ ፈንታዋን በራሷ አቅም ለመወሰን የምታደርገውን የጋራ ጉዞ የሚያጠናክር ታላቅ ዕድል ነው።
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version