Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ የንግድ ልማት ፎረም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ የንግድ ልማት ፎረም በመጪው ሰኞና ማክሰኞ በአዲስ አበባ ይሄዳል አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ።

ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ፤ ፎረሙ “የአፍሪካን የወጪ ንግድ በጥራት መገንባት” በሚል መሪ ሃሳብ ይሄዳል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ባስመዘገበቻቸው የኢኮኖሚ ውጤቶች ለፎረሙ አስተናጋጅነት እንድትመረጥ እንዳስቻላትም በመግለጫው ጠቅሰዋል።

በፎረሙ ማዕቀፍ የተለያዩ ኤግዚቢሽኖች፣ የፓናል ውይይቶች፣ እንዲሁም ከንግድና ቢዝነስ ጋር የተያያዙ የጎንዮሽ ስምምነቶችና ውይይቶች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።

የትሬድ ማርክ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢር በበኩላቸው፤ የፎረሙ ዋነኛ ትኩረት የአፍሪካን የንግድ ተወዳዳሪነት ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ለማሳካት በመሠረተ ልማት፣ በምርት ጥራት፣ በኢንቨስትመንትና በቀጣናዊ ትብብር የሚደረጉ ጥረቶችን በተቀናጀ መልኩ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ፎረሙ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና በትሬድ ማርክ አፍሪካ ትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ከኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያና ኡጋንዳ ጨምሮ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮችና የዘርፉ ተዋናዮች ይሳተፋሉ።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ልማት ድርጅት ከትሬድ ማርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “ትረስት ኢን ትሬድ” የተሰኘው አህጉራዊ ሪፖርትም በፎረሙ ወቅት ይፋ እንደሚደረግ ተመላክቷል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version