Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲስ አበባ ታላላቅ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟን አሳድጋለች – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ ታላላቅ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟን አሳድጋለች አሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ።

የ2019 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሦስት የመነሻ ቦታዎች፣ ‘ሩጫዬ ቀለሜ’ በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም እንዲጎለብትና እንዲያድግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ሁነት ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት ቱሪዝም ሁነቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ጥቅም ልታገኝ የምትችልበት ሰፊ አቅም እንዳላትም ገልጸዋል።

እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ ሁነቶች ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውንና እሴቶቻቸውን የሚያንጸባርቁበት እንዲሁም ዜጎች በመንፈስ ጠንካራና በአካል ጤናማ እንዲሆኑ የሚያበረታቱ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

ሚኒስትሯ ተሳታፊዎች ሩጫውን በማጠናቀቅ፣ ውድድሩ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ መድረክ ትልቁ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ እንዲሆን ለሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የ2019 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በመጪው እሁድ ሕዳር 13 ቀን በመስቀል አደባባይ 60 ሺህ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ይካሄዳል።

በወርቅነህ ጋሻሁን

Exit mobile version