አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብልፅግና ፓርቲ አመራር ዘንድ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ።
የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለአንድ ሳምንት በአዳማ ከተማ ሲሰጥ የቆየውን የአመራር ስልጠና ዛሬ ማጠናቀቁን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።
በስልጠና መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ በብልፅግና ፓርቲ አመራር ዘንድ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፤ “እንደ ብልፅግና ፓርቲ አሁንም ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በርካታ ውጣ ውረዶችን በትእግስት እና ባለው ጥንካሬ በመሻገር ሊቆጠሩ የሚችሉ ተጨባጭ ስራዎችን መስራት መቻሉንም አስታውቀዋል።
ፓርቲው ለኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ከመስጠጥ በዘለለ የህዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ዘንድ ተወዳዳሪ መሆኑንም አንስተዋል።
ብልፅግና ታሪክን እያጠና አኩሪ ስራ የሚሰራ ፓርቲ መሆኑን ያነሱት አቶ ሽመልስ፥ ፓርቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችን እኩል ተሳታፊ ያደረገ ነውም ብለዋል።
የብግልፅግና ፓርቲ ትልቁ ግብም በተያዘው የለውጥ መንገድ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣት ህዝቡን ወደ ብልፅግና ማሻገር እንደሆነም ነው አቶ ሽመልስ ያስታወቁት።
ሁሉም ሲቪል ሰርቫንት ሁሉንም ህዝብ በትክክል ማስተናገድ አለበት ያሉት አቶ ሽመልስ፥ የኦሮሚያ ክልል ያለውን የውሃ ሀብትም በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው፤ ይህ የብልፅግና ጎዳና ነውም ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፥ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብን ተጠቃሚነት ማእከል ባደረገ መልኩ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችም በአመራር ጥበብ እና በብልፅግና ፓርቲ አመራር ብስለት መፍትሄ እንደሚሰጠውም ገልፀዋል።
አመራሩ ባገኘው ስልጠና በመጠቀም በሁሉም ነገር የተመቸች እና ሁሉንም አቃፊ የሆነች ሀገር መገንባት ላይ ጠንክሮ መስራት አለበት ብለዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

