Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመደመር መንግሥትን የሰላምና የልማት ርምጃዎች የካዱ ውንጀላዎች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የዛሬን ብቻ ሳይሆን የትውልድን መሻትና ዘላቂ ጥቅም ያገናዘቡ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ፤ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እየመራ ይገኛል፡፡
ይህ የልማት ጉዞ ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ መልካም ጅምር ቢሆንም፤ ከሕዝብና ከሀገር እየነጠቁ ለራሳቸው ማጋበስ ለለመዱ ጥቅመኞችና የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን መርዶ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
እንደ ህገወጡ ህወሓት ያሉ ጸረ ሕዝብ ኃይሎች የኢትዮጵያን እድገትና የሕዝቦቿን ህይወት መሻሻል ሲመለከቱ ዐይናቸው ይቀላል፤ ለዚህም ነው መሬት ላይ ካለው እውነታ በተቃራኒ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችንና ክሶችን የሚያሰሙት፡፡
ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ከመንግሥትና ከተቀረው እህትና ወንድም ሕዝቦች ለመነጠል በማሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለትግራይ ሕዝብ ጥላቻ እንዳላቸው አስመስሎ የሚያቀርባቸው የቅጥፈት ክሶች ለዚህ መሳያ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንጻሩ የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩል መልማትና አብሮ ማደግ እንዳለበት በጽኑ የሚያምኑ ስለመሆናቸው በተለያዩ ወቅቶች ያደረጓቸው ንግግሮችና ያከናወኗቸው ተግባራት ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለትግራይ ሕዝብ ባደረጓቸው ንግግሮች ሕዝቡ ሰላምንና ልማትን የሚሻ፤ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመተባበር ለማደግ የሚፈልግ መሆኑን ከመመስከር ተቆጥበው አያውቁም፡፡
የትግራይ ሕዝብ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደቱ ውስጥ ንቁ ተዋናይ መሆን እንዳለበት ደግመው ደጋግመው ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች የትግራይ ሕዝብ በሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ የሚያድግበትን ሁኔታ ለመወሰን ለሚያበረክተው ሚና እውቅና የሰጡና ህዝቦችን የሚያጋምዱ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የትግራይ ሕዝብ ለሰላምና ልማትም የታገለ ሕዝብ መሆኑን በማውሳት ዳግም ለጦርነትና ለውድመት መዳረግ እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሕዝቡ በየዘመናቱ ለሀገሩ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን በማውሳት፤ ጦርነቱ ጉዳት ያደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች በፍጥነት መልሶ ለመገንባት መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ደጋግመው ቃል ገብተዋል።
የትግራይን ክልል ጉዳይ ከኃይል ይልቅ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች መካከል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተጠቃሽ ሲሆን፤ መንግሥት ግጭቶችን ያለ አንድም ጥይት በውይይት ለመፍታት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ያረጋገጠበት ነው።
ከስምምነቱ በኋላ መንግሥት በክልሉ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክ፣ የኤሌክትሪክና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር እንዲሁም ነዳጅና መሰረታዊ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ክልሉ በመላክ ለክልሉ ሕዝብ ያለውን ተቆርቋሪነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ሕዝቡ ዘላቂና ሰላምና ልማት እንደሚገባው ከመግለጽ ባሻገር፤ በክልሉ የወሰዳቸው የመልሶ ግንባታ ተጨባጭ ርምጃዎች የውንጀላው ተገላቢጦሽ ናቸው፡፡
ህገወጡ የህወሓት ቡድን ዳግም ካደረሰው ውድመት በኋላም የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የባለአደራ አስተዳደር በማቋቋም በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ጸረ ሕዝብ በሆነው ህገወጥ ቡድን የወደሙ መሠረተ ልማቶችን የመጠገን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን የማስጀመር እንዲሁም የሕዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስቻይ መደላድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡
እነዚህ ርምጃዎች የመደመር መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ደህንነት የሚገደውና በክልሉ ልማት ሳይረጋገጥ የሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ሙሉ በሙሉ ሊረጋገጥ እንደማይችል በውል የተረዳ ስለመሆኑ አስረጂ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ያስተላለፏቸው መልዕክቶችና በእርሳቸው መሪነት የተወሰዱ የሰላም ርምጃዎች ለክልሉ ሕዝብ ልማትና ብልጽግና፣ በሕዝቦች መካከል የጋራ ጥቅምን፣ ትብብርን እና አብሮነትን ለማጠናከር ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር ገልጠዋል፡፡
ይህም እንደ ህገወጡ ቡድን መሰረተ ቢስ ውንጀላ የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚያለያይ ሳይሆን፤ ይበልጥ የሚያስተሳስር ነው።
የመደመር መንግሥት መሻት አንዱን ሕዝብ ከሌላው በማራቅ ሳይሆን በእኩልነት፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ በመተማመንና ለጋራ ልማት በማሳተፍ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እውን ማድረግ ነው፡፡
በምሕረት ደምሴ
Exit mobile version