አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት፣ ለጋራ ልማት እና ትብብር መልህቅ የሆነች ሀገር ናት። በቆዳ ስፋቷ፣ በሕዝብ ብዛቷ፣ በታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖዋ እንዲሁም እያደገ በመጣው ኢኮኖሚያዊ አቅሟ ኢትዮጵያ የቀጠናው ወሳኝ ኃይል ሆና ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ወሳኝ ሚና በየዘመናቱ በመንግሥታት መለዋወጥ ውስጥ እንኳን ሳይናወጥ የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስና ዘመናዊ መልክ ይዞ ተጠናክሯል። ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት የምታበረክተው አስተዋጽኦ በተግባር የተመሰከረ ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጥላ ሥር ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ፣ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የከፈለው መስዋዕትነት ታሪካዊ ነው።
እንዲሁም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል በሚገኘው የአብዬ አካባቢ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በመንግሥት እየተከናወኑ የሚገኙ የሰላም ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ተጠናክሯል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቀጣናው መልህቅነትን ሚና ከተለምዷዊ ወታደራዊና የሰላም ማስከበር አቅም ባሻገር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና ሀገር በቀል ርዕዮተ ዓለም ተሸጋግሯል።
ኢትዮጵያ ከውኃ፣ ከነፋስና ከፀሐይ የምታመነጨውን ንጹሕ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ ቀጣናውን በኃይል እያስተሳሰረች ትገኛለች።
ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የቀየረው ይህ የኃይል አቅርቦት፤ ጎረቤት ሀገራት የኃይል እጥረት እንዳይገጥማቸው ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት የጋራ ተጠቃሚነትን እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው።
ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ እያስመዘገበች ያለችው ሁለንተናዊ ለውጥ ለቀጣናው አዲስ የልማት ተምሳሌት ሆኗል።
በመደመር ፍልስፍና የሚመራው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግል ዘርፉን በማነቃቃት፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ አእማዶችን በማብዛትና ከቀጠናዊ ገበያ ጋር በማስተሳሰር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖ ከፍ እያደረገ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑት ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርም አዲስ የከተማ ኑሮ ዘይቤን በመፍጠር ለአካባቢው ሀገራት ዓርዓያነት ያለው መልካም ተሞክሮ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር፣ በዲፕሎማሲ፣ በንጹሕ ኃይል አቅርቦትና በፈጣን የልማት ሥራዎች ልምዷን በማጠናከር፣ አዳዲስ የልማትና የዲፕሎማሲ አማራጮችን ይዛ በመቅረብ የምሥራቅ አፍሪካ የማይናወጥ መልህቅነቷን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በዮናስ ጌትነት

