Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጤና ሉዓላዊነት፤ የኢትዮጵያ አዲስ የልማት አቅጣጫ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ ከሕዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በሚካሄደው 5ኛው የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ኮንፈረንስ አፍሪካን እና መላውን ዓለም በአዲስ አበባ በታላቅ ደስታ ታስተናግዳለች ብለዋል።

በጋራ በመሆን የጋራ መሻቶቻችንን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንቀይር፤ የበለጠ ጤናማ እና ተግዳሮቶችን መቋቋም የምትችል አፍሪካን እንገንባ ፤ አፍሪካ ዝግጁ ናት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

‎«አፍሪካ ዝግጁ ናት!» የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት÷ ጤናማና ተግዳሮቶችን መቋቋም የምትችል አህጉር መገንባት የሚለውን የጋራ ምኞት የሚያንጸባርቅ ነው።
‎
‎ይህ መልዕክት የተሻለ የጤና አገልግሎት ለዜጎች ከማቅረብ ባለፈ፣ አፍሪካ የራሷን የጤና ችግሮች በራሷ አቅም፣ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በምርት አቅም እንድትፈታ የሚጠይቅ ነው።
‎
‎የመደመር መንግሥት በጤናው ዘርፍ የያዘው አቅጣጫ ጤናን ከሕክምና ተቋማትና ከሕመም ማከም ጋር ብቻ የሚያያዝ ጉዳይ አድርጎ አይመለከትም።
‎
‎እሳቤው ጤና የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት፣ የሀገር ልማት መሠረት እና የሰው ኃይል ምርታማነት መገለጫ መሆኑን ያስቀድማል።
‎
‎በዚህም መሠረት የጤና ፖሊሲው በሽታን ከመከላከል ጀምሮ ታካሚዎችን በወቅቱ አክሞ ማዳን፣ የጤና ችግሮች ሲከሰቱ በተቀናጀ ሁኔታ ምላሽ መስጠት፣ የጤና ሥርዓቱን የመቋቋም አቅም ማሳደግና የሕክምና ጥራትን ማሻሻል ያካትታል።
‎
‎ይህ አቅጣጫ ጤናን ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ፣ ከቤተሰብ እስከ ሀገር የሚዘልቅ የልማት ጉዳይ አድርጎ ያስቀምጠዋል። በተለይም የመከላከል፣ የማከምና የማገገሚያ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ ማጠናከር የሥርዓቱ ቁልፍ አቅጣጫ ነው።
‎
‎ከመድኃኒት ገዢነት ወደ አምራችነት
‎
‎ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያ አብዛኛውን የመድኃኒት ፍላጎቷን ከውጭ በማስገባት ስትሸፍን ቆይታለች። ይህ በውጭ ምንዛሪ ላይ ጫና ከመፍጠሩ ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መዛባት ወቅት የመድኃኒት ተደራሽነትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነበር።
‎
‎ይህን ተግዳሮት ለመቀየር መንግሥት የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች የሀገር ውስጥ ምርትን ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው የልማት መስኮች አንዱ አድርጎ ይዟል። በዚህ ረገድ የቂሊንጦ የመድኃኒት ኢንዱስትሪ ፓርክ ለዘርፉ ልማት የተዘረጋው አንዱ ቁልፍ መሠረተ ልማት ነው።
‎
‎በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ እንደ ኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ማኑፋክቸሪንግ፣ አዲስ ፋርማሲዩቲካል፣ ካዲላ ፋርማሲዩቲካል እና ሌሎች የመድኃኒት አምራች ተቋማት የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው።
‎
‎በተጨማሪም የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የቁጥጥር ሥርዓትን ማጠናከር፣ የምርቶችን ጥራትና ደኅንነት ማረጋገጥ እንዲሁም የአምራች ተቋማትን አቅም ማሳደግ በዘርፉ ለሚታየው ለውጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው።
‎
‎ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ያላት እምቅ አቅም በሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ ወደ አህጉራዊ የጤና አገልግሎት ማዕከልነት የሚያደርስ ዕድል አለው።
‎
‎በስትራቴጂካዊ የጂኦግራፊ አቀማመጧ፣ በአየር ትራንስፖርት ትስስሯ፣ በሰው ኃይል አቅሟና በተለያዩ የተፈጥሮ መስህቦቿ ኢትዮጵያ በጤና ቱሪዝም ዘርፍ የምትጠቀምበት በርካታ ዕድሎች አሏት።

‎ይህንን አቅም በመገንዘብ መንግሥት የጤና ቱሪዝምና የጤና አገልግሎት ልማትን ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማበረታታት፣ ዘመናዊ የሕክምና ተቋማትን ማስፋፋትና ለዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥን የሕክምና አገልግሎት መፍጠር ላይ ትኩረት እየሰጠ ነው።
‎
‎ኢትዮጵያ የሕክምና መዳረሻ ብቻ ሳትሆን የጤና ቱሪዝምን ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከተፈጥሮ መስህቦችና ከዘመናዊ አገልግሎት ጋር አቀናጅታ የምታቀርብበት አቅምም ገንብታለች።
‎
‎ይህ እውን እንዲሆን ግን የሕክምና ጥራት፣ የባለሙያ ብቃት፣ የታካሚ ደኅንነት፣ የመሠረተ ልማትና የዓለም አቀፍ እውቅና ግንባታ ወሳኝ ናቸው።

Exit mobile version